ኢትዮጵያ እና አየርላንድ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በትብብር መንፈስ ዳግም ማደስ አለባቸው - አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና አየርላንድ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በትብብር መንፈስ ዳግም ማደስ አለባቸው - አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ
አዲስ አበባ ሐምሌ 7/2015 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ እና አየርላንድ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በትብብር መንፈስ እንደገና ማደስ እንደሚገባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።
አምባሳደር ምስጋኑ ከአየርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋና ፀሐፊ ጆሴፍ ሃኬት ጋር የሁለቱን አገራት ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ተወያይተዋል።
ኢትዮጵያ እና አየርላንድ ለረጅም ጊዜ የቆየ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው አምባሳደር ምስጋኑ አውስተዋል።
ይህን ግንኙነት በትብብር መንፈስ በድጋሚ ማደስ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ ለዋና ፀሐፊው ኢትዮጵያ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸው አየርላንድ የመልሶ ግንባታ እና መልሶ ማቋቋም ጥረቶችን እንድትደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።
ጆሴፍ ሃኬት በበኩላቸው አየርላንድ የኢትዮጵያ መንግስት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እያደረገች ያለቻቸውን ጥረቶች እንደምትደግፍ ገልጸዋል።
አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን መድረኮች ያላትን ትብብር የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።