የወራቤ -ቦዠባር የአስፋልት ኮንክሪት መንገድን በሁለት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው-የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
የወራቤ -ቦዠባር የአስፋልት ኮንክሪት መንገድን በሁለት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው-የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር
አዲስ አበባ ሐምሌ 7/2015(ኢዜአ)፡- የወራቤ-ቦዠባር የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ፕሮጀክትን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ገለጸ፡፡
የወራቤ-ቦዠባር የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ፕሮጀክት 41 ነጥብ 3 ኪ.ሜ ርዝመት ሲኖረው ስልጤ ዞን፣ ወራቤ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም አሊቾና አካባቢውን የሚያገናኝ ነው፡፡
የመንገድ ግንባታ ሥራው ከዚህ ቀደም የነበረው አገር በቀል ተቋራጭ የስራ አፈጻጸም ጋር ተያያዞ ውሉ እንዲቋረጥ መደረጉም ነው የተገለጸው።
አሁን ላይ የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት የስራ ውል ወስዶ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ እየሰራ ይገኛል፡፡
ፕሮጀክቱ ከ2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት እየተከናወነ ይገኛል፡፡
ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር፣ ከስልጤ ዞን የስራ ኃላፊዎች እና የአካባቢው ማህበረሰብ ተወካዩች በስፍራው በመገኘት የመንገድ ግንባታ ሒደቱን ተመልክተዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ደጀኔ ፍቃዱ፤ ፕሮጀክቱ በስራ ተቋራጮች የአፈፃጸም ውስንነት እና ተያያዥ ችግሮች ሲጓተት መቆየቱን ገልጸዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ ቅሬታ የሆነውን የመንገድ ግንባታ ስራ፤ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የስልጤ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ቀድሩ አብደላ ፕሮጀክቱ በግንባታ ስራ ተቋራጮች የአፈፃጸም ውስንነት በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ ባለመቻሉ ከፍተኛ የህዝብ ቅሬታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ፤ፕሮጀክቱ የማህበረሰብ ጥያቄ እየሆነ መምጣቱን ከግምት በማስገባት ግንባታውን እንደገና ማስጀመሩን አድንቀዋል።
የዞኑ ማህበረሰብ እና አስተዳደርም በግንባታ ሂደቱ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር መብት አድማስ ፤ የመንገድ ግንባታ ስራውን በተያዘለት በጀት፣ ጥራትና ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የመንገድ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የአካባቢውን ማህበረሰብ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማሳለጥ አዎንታዊ ፋይዳ ይኖረዋል።