የስፖርቱ ማህበረሰብ እና የመዲናው ወጣቶች በእንጦጦ ፓርክ አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ - ኢዜአ አማርኛ
የስፖርቱ ማህበረሰብ እና የመዲናው ወጣቶች በእንጦጦ ፓርክ አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ
አዲስ አበባ ሀምሌ 7/2015(ኢዜአ)፡- የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከከተማው የስፖርት ማህበረሰብና የመዲናው ወጣቶች ጋር በመሆን አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ።
የስፖርት ቤተሰቡ "ነገን ዛሬ እንትከል" በሚል መሪ ሀሳብ በእንጦጦ ፓርክ ከ21 ሺህ በላይ ችግኞችን በዛሬው ዕለት ተክለዋል።
በተከላው የስፖርት ቤተሰቦች፣ የቢሮው ሰራተኞች ፣አንጋፋ አትሌቶች እና ታዋቂ ስፖርተኞችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተው አሻራቸውን አኑረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን፤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የስፖርት ቤተሰቡና ወጣቱ ለሀገር ልማት የሚከናወኑ ቁልፍ ስራዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ነው።
ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም 500 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ቀን ለመትከል ለተያዘው እቅድ ቢሮው አስፈላጊ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልፀዋል።
በችግኝ ተከላው ላይ የተሳተፉት ኮማንደር አበበ መኮንን፤ እንደ ሀገር እየተተገበረ ያለው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖን ከመከላከል አንፃር የላቀ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ተናግረዋል ።
ደንና አትሌት የተለየ ትስስር ያላቸው በመሆኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለስፖርት ቤተሰቡ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም አንስተዋል ።
አትሌቶች ልምምድ ብቻ ሳይሆን ንፁህ አየር ማግኘታቸውም ለሚያስመዘግቡት ውጤት አስፈላጊ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ይህንኑ በመረዳትም እንደሀገር በተጀመረው የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ከመሳተፍ ባለፈ የተተከሉት ችግኞችን በመንከባከብ የጎላ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቃል ነው ያሉት።