ቀጥታ፡

ከ353 ሺህ በላይ አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆኑ-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት

አዲስ አበባ ሐምሌ 7/2015 (ኢዜአ):- በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 353 ሺህ 144 አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑት አዳዲስ ደንበኞች መካከል 96 በመቶ የሚሆኑት የድህረ ክፍያ ደንበኞች መሆናቸውም ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም አዳዲስ የገጠር ከተሞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በተሰራው ስራ 125 ከተሞችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተገልጿል፡፡

አዳዲስ ከተሞችንና መንደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ 1 ሺህ 236 ነጥብ 58 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ እና 1ሺህ 891 ኪሎ ሜትር ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ እንዲሁም 405 ትራንስፎርመሮችን የመትከል ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

ተቋሙ በተያዘው በጀት ዓመት ከባለፈው በተሻለ አዲስ ኃይል ፈላጊ ደንበኞችን፣ ከተሞችን እና የገጠር መንደሮችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም