ቀጥታ፡

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የኢትዮጵያዊያንን የመረዳዳት እሴት በማጎልበት አገሩን የሚወድ ትውልድ ለመፍጠር እያገዘ ነው- አቶ ርስቱ ይርዳው

 

ሐዋሳ ሐምሌ 6/2015 (ኢዜአ) የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የኢትዮጵያዊንን ቱባ የመረዳዳት እሴት በማጎልበት አገሩን የሚወድ ትውልድ ለመፍጠር እያገዘ ነው ሲሉ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው ገለጹ።

በክልሉ የ2015 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል።

ፕሮግራሙን በይፋ ያስጀመሩት አቶ ርስቱ ይርዳው በዚህ ጊዜ እንደተናገሩት ኢትዮጵያዊያን የቆየ የመረዳዳትና የበጎነት ባህል አላቸው።

ከአገራዊ ለውጡ በኋላ እየተከናወነ ያለው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ነባሩን የመረዳዳት እሴት በማጎልበት አገሩን የሚወድ ትውልድ እንዲፈጠር እያበረከተ ያለው አስተዋጾ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

"በበጎ ፍቃድ ሌሎችን በማገልገል ውስጥ የምናሳየው ሰብአዊነት ትልቅ ጸጋ ነው" ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፣ ይህ የዳበረ ባህል የኢትዮጵያ ዋስትና መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ ወጣቶች ካለፉት ዓመታት ጀምሮ እያከናወኑ ባሉት የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ለተለያዩ የማህበረሰቡ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ ተግባራት መፈጻማቸውንም አቶ ርስቱ ገልጸዋል።

ከስጦታዎች ሁሉ የሚበልጠውን ደም ከመለገስ ጀምሮ በወጣቶቹ የተከናወኑ ተግባራት መኖራቸውን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ "ባለፉት አራት ዓመታት በክልሉ ከ10 ሺህ 600 በላይ የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳትና ግንባታ ተደርጓል" ብለዋል።


 

የበጎ አገልግሎት ሥራው በገንዘብ ሲተመን ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ በትምህርት፣ በአረንጓዴ አሻራና በሌሎች መስኮች የተከናወኑ የበጎ አገልግሎት ተግባራት ለበርካታ ዜጎች እፎይታን በመስጠት በኩል የጎላ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።

አረጋዊያንን መደገፍና የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል በበጀት ዓመቱ በልዩ ትኩረት የሚከናወን ተግባር መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።

እንደ አቶ ርስቱ ገለጻ፣ ባለፈው ዓመት ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን የመገንባትና የመጠገን ስራ የተሰራ ሲሆን በቀጣይም በህዝብ ንቅናቄ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ከዚህ ቀደም የተከናወኑ ተግባራት መተባበርና መቀናጀት ከተቻለ የበለጠ መስራት እንደሚቻል ያመላከቱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ መላው የክልሉ ህዝብ በዚህ በጎ ተግባር እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

በክልላዊ የክረምት በጎ ፈቃድ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የማዕድን ሚኒስትሩ ኢኒጂነር ሃብታሙ ተገኝ በበኩላቸው "መረዳዳትና መደጋገፍ የኢትዮጵዊያን የቆየ ባህል፤ በጎ ተግባር ደግሞ የሰብአዊነት የሞራል ሚዛን ውሃ ልክ ነው" ብለዋል።

ወጣቶች ጊዜና ጉልበታቸውን ተጠቅመው ሃገራቸውን በማገልገል ኢትዮጵያን ከሚገጥማት ፈተና ማሳለፍ እንደሚችሉም አመልክተዋል።

"በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወጣቶች ከአካባቢያቸው አልፈው በመስራት የመደጋገፍ ባህልን ማሳደግና በየአካባቢው ያለውን እምቅ አቅም ወደ ልማት በመቀየር የሀገርን ተስፋ ማለምለም አለባቸው" ሲሉም ገልጸዋል።

በክልሉ በየዓመቱ በተከናወኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች እመርታዊ ለውጥ መመዝገቡን የጠቀሱት ደግሞ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘሪሁን እሸቱ ናቸው።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ወጣቶች ዴሞክራሲዊ መብቶቻቸውን እንዲለማመዱና በመንግስት ያልተሸፈኑ የህብረተሰቡና የመንግስት ፍላጎቶችን በማሟላት የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ማስቻሉንም ተናግረዋል።

በዘንድሮ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በ13 ዘርፎች በመሳተፍ ከ7 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት ያከናውናሉ ብለዋል።

በዚህም ከመንግስትና ከህዝብ ሊወጣ የሚችልን 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚያድን የበጎ ተግባር አገልግሎት እንደሚከናውኑ ጠቅሰዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በከፍተኛ አመራሮችና ወጣቶች ቤታቸው መታደስ የጀመረው በሶዶ ከተማ የሰላም መንደር ነዋሪዋ ወይዘሮ አበራሽ አልቤ በበኩላቸው፣ የሚኖሩበት ቤት አድሳት በመጀመሩ በእጅጉ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

አቅም ደካማ የሆኑት ወይዘሮዋ በቀን ሥራ በሚያገኙት ገቢ እንደሚተዳደሩና ቤታቸውን ለማደስ አቅም እንደሌላቸው ተናግረው፣ ስለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

በመርሀ ግብሩ ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ ወጣቶችና ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን የደም ልገሳ፣ የችግኝ ተከላና የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ መርሃ ግብር ተከናውኗል።

All reactions:

22

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም