በወልዲያ ከተማ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
በወልዲያ ከተማ የተገነቡ መሰረተ ልማቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ
ወልዲያ ሐምሌ 6/2015(ኢዜአ) በወልዲያ ከተማ አስተዳደር ከ20 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ በመልሶ ግንባታ ፕሮግራም የተገነቡ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋምና የእንስሳት ክሊኒክ ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ።
የከተማው ውሃ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ሞገሰ እንዳሉት በጦርነት የወደሙ ተቋማትን ለመገንባት በተያዘው የመልሶ ግንባታ ፕሮግራም የውሃ ተቋሙ መልሶ መገንባት ተችሏል።
በዚህም 15 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ በፀሐይ ሃይል የሚሰራ የውሃ ተቋም መልሶ በመገንባት በከተማው የሚስተዋለውን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማቃለል ያስቻለ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህ ፕሮጀክት ቀደም ሲል በኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎቱ ይሰጥ የነበረውን በፀሐይ ሃይል በመተካት ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ለአገልግሎት እንዲበቃ ተደርጓል።
የግንባታው ወጪ በመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተገኘ ሲሆን የውሃ ተቋሙ በጦርነቱ ጉዳት ደርሶበት በመልሶ ማቋቋም ፕሮግራም የተሰራ ነው ብለዋል።
የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ በበኩላቸው በፀሐይ ኃይል የሚሰራው የውሃ ተቋም በሰከንድ 27 ሊትር ውኃ ለከተማው ነዋሪዎች ማድረስ የሚያስችል አቅም አለው።
የከተማ አስተዳደሩ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማስፋት በቀጣይም ተጨማሪ ስራ እንደሚሰራ ጠቅሰው፤ የከተማውን የንፁህ ውሃ ሽፋኑን ከ52 በመቶ ወደ 70 በመቶ የሚያደርስ ፕሮጀክት ለመገንባት ከወልድያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የቦታ ርክክብ መደረጉን ገልፀዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በከተማውና በዙሪያው ላሉ ወረዳዎች አገልሎት የሚሰጥ የእንስሳት ክሊኒክ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱን ተናግረዋል።
"ክሊኒኩ በወልዲያ፣ ጉባላፍቶ፣ ራያ ቆቦ እንዲሁም በሐብሩ ወረዳዎች ለሚገኙ አቅራቢያ ቀበሌዎች አገልግሎት ይሰጣል" ያሉት የወልዲያ ከተማ እንስሳትና አሳ ሃብት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ በላይ ገሰሰ ናቸው።
በመልሶ ማቋቋም ፕሮግራሙ የተገነባው ክሊኒክ በቀን ከ120 በላይ ለሚሆኑ እንስሳት ህክምናን ጨምሮ የማዳቀልና ሌሎች አገልግሎቶችን እንደሚሰጥም አስረድተዋል።
በወልዲያ ከተማ የቀበሌ 10 ነዋሪ አቶ በላይ መላኩ በሰጡት አስተያየት ዛሬ ለምረቃ የበቃው የንጹህ መጠጥ ውሃ የህብረተሰቡን ጥያቄ የመለሰ ነው።
''የውሃ ተቋሙ በሃይል አቅርቦት እጥረት ምክንያት ገጥሞን የነበረውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር የፈታ ነው'' ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ የሺወርቅ ሲሳይ ናቸው።
ቀደም ሲል የውሃ አቅርቦቱ የኤሌክትሪክ ሀይል ሲቋረጥ አብሮ እንደሚቋረጥ አስታውሰው፣ አሁን በፀሐይ ሃይል እንዲሰራ መደረጉ ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታ ነው ብለዋል።
የንፁህ መጠጥ ውሃ ተቋሙና የእንስሳት ክሊኒኩ ቀደም ሲል በጦርነቱ ጉዳት ደርሶባቸው የቆዩና አሁን በመልሶ ማቋቋም ፕሮግራም የተሰሩ ናቸው።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የወልዲያ ከተማ አስተዳደር አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።