በቀጣይ አሥር ቀናት በአንዳንድ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ ስለሚኖር ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል -የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
በቀጣይ አሥር ቀናት በአንዳንድ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ ስለሚኖር ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል -የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ ሐምሌ 6/2015 (ኢዜአ) በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በአንዳንድ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ ስለሚኖር ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች መደበኛ ዝናብ እንደሚኖር ገልጿል።
በተለይም አብዛኛው የትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ሲዳማ ክልሎች አካባቢዎች መደበኛ ዝናብ ያገኛሉ ብሏል።
ይህም በአካባቢዎቹ ላይ እየተከናወነ ለሚገኘው የግብርና እንቅስቃሴ በጎ ሚና የሚጫወት መሆኑንም አመላክቷል።
በትንበያው መሰረት የዝናብ ስርጭትና መጠኑ የተሻለ ስለሚሆን የአፈር እርጥበት ለግብርና እንቅስቃሴ ለማከናወን ለተዘሩ ሰብሎች ውሃ ፍላጎት ለማሟላትና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የመኖ ሳር ልምላሜ በጎ ተጽዕኖ እንደሚኖረው አስታውቋል።
በኦሮሚያ ክልል በጅማ፣ ኢሉባቦር፣ አራቱ የወለጋ ዞኖች፣ በሁሉም ሸዋ ዞኖች፣ በምዕራብ ሐረርጌ፣ አርሲና ምዕራብ አርሲ ዞኖች ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛሉ ተብሎ ይገመታል።
በተመሳሳይ በአማራ ክልል ምዕራብና ምሰራቅ በጎጃም፣ አዊ፣ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ ባህዳር ዙሪያ፣ ዋግ ህምራ፣ ሰሜንና ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ከመደበኛ የተቀራረብና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛሉ።
በሌላ በኩል በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብና ሲዳማ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ያመላክታሉ ብሏል።
በዚህም የወንዞች ከገደብ በላይ መሙላት ሊከሰት ስለሚችል ህብረተሰቡና የሚመለከታቸው አካላት በሰው ህይወትም ሆነ በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አስፋለጊውን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
ተፋሰሶች የተሻለ እርጥበት የሚኖራቸው ሲሆን ይህም በዓባይ፣ ተከዜ፣ ባሮ፣ አኮቦ፣ ኦሞ፣ ጊቤ፣ አዋሽ፣ ገናሌና ዳዋ፣ ዋቢ ሸበሌ የውሃ ክምችት ላይ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ጠቁሟል።
ነገር ግን በዓባይ፣ በባሮ አኮቦና እና በአዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎች ላይ በሚኖራቸው ከባድ መጠን ያለው እርጥበት ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊኖር ስለሚችል ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ሲል አሳስቧል።
በሌላ በኩል በባሌ፣ በምስራቅ ሀረርጌ፣ በድሬዳዋ፣ በሀረሪ፣ በጅግጅጋና በአፋር ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ላይ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር ኢንስቲትዩቱ ገልጿል።
ከኦሮሚያ ክልል ቦረናና ጉጂ፣ ከሶማሌ ክልል ሊበን፣ አፍዴር፣ ሸበሌ፣ ቆራሂና ዶሎ ዞኖች፣ የአፋር ክልል አብዛኛው አካባቢ እንዲሁም የደቡብ ኦሞና የሰገን ህዝቦች አካባቢዎች አልፎ አልፎ ከሚኖራቸው የደመና ሽፋን በስተቀር በአብዛኛው ደረቅ ሆነው እንደሚቆዩ የኢንስቲትዩቱ ትንበያ ያመለክታል።