የ500 ሚሊየን ችግኝ ተከላ መረጃን ከ9 ሺህ 500 ጣቢያዎች በቀጥታ ለዓለም ተደራሽ የሚያደርግ የቴክኖሎጂና የካርታ ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የ500 ሚሊየን ችግኝ ተከላ መረጃን ከ9 ሺህ 500 ጣቢያዎች በቀጥታ ለዓለም ተደራሽ የሚያደርግ የቴክኖሎጂና የካርታ ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ ሐምሌ 6/2015 (ኢዜአ) የ500 ሚሊየን ችግኝ ተከላ መረጃን ከ9 ሺህ 500 ጣቢያዎች በቀጥታ ለዓለም ተደራሽ የሚያደርግ የቴክኖሎጂና የካርታ ዝግጅት መደረጉን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ- ግብር አስተባባሪ ግብረ-ኃይል ገለፀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያውያን በመጪው ሰኞ ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል በነቂስ እንዲወጡ መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወቃል።
በዕለቱ ለሚካሄደው የችግኝ ተከላ 361 ሺህ 415 ሄክታር መሬት በመላው ሀገሪቱ ዝግጁ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር ገልጿል።
የችግኝ ተከላውን ለመላው ዓለም በቀጥታ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚመራው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አስተባባሪ ግብረ-ኃይል ገልጿል።
በሚኒስቴሩ የኤሌክትሮኒክ መንግሥት ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚና የግብረ-ኃይሉ አስተባባሪ ዶክተር ኢንጂነር አብዮት ሲናሞ፤ በአንድ ጀምበር በመላው ኢትዮጵያ የሚካሄደውን የችግኝ ተከላ ሂደትና መረጃ በአግባቡ መሰብሰብና ለዓለም ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ዲጂታል ቋት መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
GREENLEGACY.ET የተሰኘ ድረ-ገፅ መዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ በዚህም ትክክለኛውን መረጃ ማንኛውም ሰው በዕለቱ ማግኘት ይችላል ነው ያሉት።
በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ መረጃው በአግባቡ የሚሞላበትን ዘዴ፣ የቦታዎችን ስፋት፣ ቅርፅና ልዩ አካባቢ የመለየትና በአግባቡ በካርታ የማስቀመጥ ሥራ መሠራቱን ጠቅሰዋል።
በስፔስ ሳይንስና ጂኦ-ስፓሻል ኢንስቲትዩት የካርታ ሥራ መሪ ሥራ አስፈጻሚና የግብረ-ኃይሉ አባል ቴዎድሮስ ካሳሁን በበኩላቸው፤ እስካሁን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል 9 ሺህ 500 የችግኝ መትከያ ጣቢያዎች የካርታ መረጃ መመዝገቡን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ የችግኙን ዓይነት እና የተተከለበትን ቦታ መረጃ በአግባቡ የሚያሳይ የጂኦ- ስፓሻል መረጃ ሥርዓት መዘረጋቱን ገልፀዋል።
የይዞታ ካርታው አጠቃላይ ችግኝ ተከላው ከተጀመረበት ቦታ በማጠቃለያው እስከተደረሰበት ያለውን ስፋት በግልጽ በሚያሳይ መልኩ መዘጋጀቱንና ለዚህም የሚረዳ መረጃ መሰብሰቡን ጠቁመዋል።
የግብረ-ኃይሉ አባላት አክለውም የቴክኖሎጂ ሥርዓቱ በዕለቱ የሚካሄደውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የዲጂታል ቋቱ ወጥ የሆነ እውነተኛ የመረጃ ምንጭ እንዲኖርና ከወረዳ ጀምሮ ሐሰተኛ ሪፖርት እንዳይኖር የማድረግ ዓላማ እንዳለው ጠቅሰዋል።
ለመንግሥት፣ ለዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ለተመራማሪዎችና ለሌላው ሕብረተሰብ ችግኞች በትክክል ያሉበትን ቦታ ለማመላከት፣ የፀደቁና ያልፀደቁትን ለመለየትና ዋቢ መረጃዎችን ለማቅረብ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
ዶክተር አብዮት የ500 ሚሊየን ችግኝ ተከላው የመረጃ መሰብሰብና ሥርጭት በዲጂታል ሥርዓቱ በቀጥታ አልያም በተረጋገጠ የስልክ መለያ እንደሚከናወን ተናግረዋል።
ለዚህም እስከ 27 ሺህ የሰው ኃይል መመደቡን ገልጸው፤ የሚተከሉ ችግኞች ዓይነትና ስም፣ የመትከያ ቦታ፣ ሰዓትና አጠቃላይ ብዛት እየተጣራ መረጃው ለዓለም ተደራሽ ይሆናል ነው ያሉት።
ለባለሙያዎች በቂ ሥልጠና መሰጠቱን ጠቅሰው፤ ሥራቸውን በኃላፊነትና በስነ-ምግባር መምራት እንዳለባቸውና የተሳሳተ መረጃ የሚልክ የትኛውም አካል ተጠያቂ እንደሚሆን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት 25 ቢሊየን ችግኞችን በመትከል ያሳየችውን ስኬት ለመድገም ሁለተኛ ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን ጀምራለች።
ለዚህም ዘንድሮ 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ሲሆን፤ እስካሁንም 3 ነጥብ 4 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውን ግብርና ሚኒስቴር መግለጹ ይታወቃል።