በኢዜአ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል--የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ - ኢዜአ አማርኛ
በኢዜአ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል--የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ
አዲስ አበባ ሐምሌ 6/2015(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የአጋርነት ሥራዎችን ማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት በዛሬው እለት ተፈራርመዋል።
የኢዜአ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ እና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል ስምምነቱን ተፈራርመዋል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ፤ በኢትዮጵያ ሚዲያ ታሪክ ኢዜአ በርካታ ውጣ-ውረዶችን አልፎ አሁን ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል።
ኢዜአ ከ80 ዓመታት በፊት ሲቋቋም ለአገር ውስጥና ለመላው ዓለም ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም የአገርን ገጽታን የመገንባት ዓላማ ይዞ መነሳቱን አስታውሰዋል።
በእነዚህ ዓመታትም ለአገር የሚጠቅሙ በርካታ ስራዎችን ከመስራት ባለፈ ለአህጉራዊ የነፃነት ትግልም የላቀ ሚና እንደነበረው ይነገራል ብለዋል።
የአገራዊ ለውጡን እውን መሆኑን ተከትሎ የኢዜአን ተጠሪነት ከማሻሻል ጀምሮ የሕግ ማዕቀፍ ለውጥ በማድረግ ጭምር በላቀ የለውጥ ሂደት ላይ መሆኑን አንስተዋል።
ኢዜአን በተለይም በአሰራርና በቴክኖሎጂ በማዘመን ረገድ የተከናወኑ ተግባራት የሚደነቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የተቋሙን አገራዊ ተልዕኮ ለማሳካት እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ያስገነዘቡት አቶ እውነቱ፤ ለዚሁ ስኬት ምክር ቤቱ አስፈላጊውን ሁሉ እገዛ ያደርጋል ሲሉ አረጋግጠዋል።
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል፤ አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የአገር ገጽታን ከመገንባት ባለፈ ትክክለኛ መረጃዎችን በሁሉም ዘንድ ተደራሽ በማድረግ አገራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ደግሞ አገራዊ የለውጥ ሥራዎችን ተከትሎ ኢዜአ በአገር ገጽታ ግንባታና ሁለንተናዊ መረጃዎችን ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ የላቀ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
የተቋሙ ስራዎች በቀጣይነትም ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ያሉት አቶ ረሻድ፤ የቤቶች ኮርፖሬሽን ከኢዜአ ጋር የሚያደርገውን የለውጥ ጉዞ አጋርነት ያጠናክራል ሲሉ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፤ ኮርፖሬሽኑ በኢትዮጵያ የለውጥ ሂደት ውስጥ በግንባታው ዘርፍ ትልቅ አስተዋጽዖ እያበረከተ ያለ ተቋም መሆኑን ገልፀዋል።
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በርካታ ተግዳሮቶችን በመቋቋም ዘመናዊ የግንባታ አሰራሮችን በመተግበር በኢትዮጵያ ማንኛውንም ስራ ማሳካት እንደሚቻል በተግባር ያሳየ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለሠራተኞቹ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ሂደት ከኮርፖሬሽኑ ጋር በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም የትብብር ስራዎቻችን ይቀጥላሉ ብለዋል።
በዕለቱም በተቋሙ የተገነባው የእንግዳ መቀበያ ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃ ሲሆን በግንባታው አስተዋጽዖ ላበረከቱ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞችም እውቅና ተሰጥቷል።