አውደ-ርዕዩ በኢትዮጵያ ጠንካራ የጤና ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን አሳይቶናል -ጎብኚዎች - ኢዜአ አማርኛ
አውደ-ርዕዩ በኢትዮጵያ ጠንካራ የጤና ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን አሳይቶናል -ጎብኚዎች
አዲስ አበባ ሐምሌ 06/2015 (ኢዜአ) በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን የጤና አውደ- ርዕይ በኢትዮጵያ ጠንካራ የጤና ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን አሳይቶናል ሲሉ ጎብኚዎች ገለጹ፡፡
የፌዴራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን እና የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን የጤና አውደ-ርዕይ ጎብኝተዋል።
ከጉብኝቱ ጎን ለጎንም የደም ልገሳ ፕሮግራም አካሂደዋል፡፡
የፌዴራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እሸቴ አስፋው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አውደ- ርዕዩ ኢትዮጵያ በሕክምና አገልግሎት፣ በሰው ኃይል ግንባታና በግብዓት አቅርቦት የደረሰችበትን ደረጃ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
በአገሪቱ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ ተንቀሳቃሽ የጤና ሕክምና ያለበትንና የላቦራቶሪ ዘርፍ የደረሱበትን ደረጃ ተመልክተናል ብለዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ደሳለኝ አምባው በበኩላቸው፤ አውደ -ርዕዩ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የደረሰችበትን የቴክኖሎጂ ደረጃ ያሳየ ነው ብለዋል።
አገሪቱ በዘርፉ በሽታን ከመከላከል ጀምሮ እስከ ሕክምና አሰጣጥ ድረስ እየሰራች ያለው ሥራ ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል፡፡
ከጎብኝዎች መካከል አቶ ተስፋዬ ሻሚየ እንዳሉት፤ አውደ-ርዕዩ አገሪቱ በጤናው ዘርፍ የደረሰችበትን የአገልግሎት አሰጣጥ እንዳውቅ አድርጎኛል ብለዋል፡፡
የቴክኖሎጂና የሰው ሃይል አቅምን ከማሳደጉ በፊት በውጭ አገር ይሰጥ የነበረውን የህክምና አገልግሎት በአገር ውስጥ መሰጠት መጀመሩም ለአገርም ለዜጎችም ኩራት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሕብረተሰቡ አውቆ አገልግሎቱን በአግባቡ መጠቀም እንዲችል መሰል ሥራዎች በተከታታይ መሠራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
አቶ ክንዴነው ካሳሁን በበኩላቸው፤ መንግሥት በተለይ የባህላዊ ሕክምናን ከዘመናዊ ጋር አስተሳስሮ ተግባራዊ ለማድረግ እየሄደበት ያለው ርቀት አበረታች ነው ብለዋል፡፡