ሴቶች በተሰማሩበት መስክ ሁሉ ተፅዕኖ ፈጣሪና ስኬታማ ለመሆን በራስ የመተማመን አቅማቸውን ማጎልበት አለባቸው - ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
ሴቶች በተሰማሩበት መስክ ሁሉ ተፅዕኖ ፈጣሪና ስኬታማ ለመሆን በራስ የመተማመን አቅማቸውን ማጎልበት አለባቸው - ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ ሐምሌ 6/2015 (ኢዜአ)፦ ሴቶች በተሰማሩበት መስክ ሁሉ ተፅዕኖ ፈጣሪና ስኬታማ ለመሆን በራስ የመተማመን አቅማቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት፣ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ከዩ ኤን ውመን ጋር በመተባበር ለሴት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የአቅም ግንባታና አመራር ጥበብ ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ልምድና ተሞክሯቸውን ባጋሩበት ወቅት እንዳሉት፤ ሴቶች ለሰላምና ልማት ትልቅ አቅም ቢኖራቸውም በዚሁ ልክ የመወሰን እድል በአግባቡ እያገኙ አይደለም።
በዓለም ላይ በተለይ ደግሞ በአፍሪካ ሴቶች ከወንዶች እኩል የመምራትና የማስተዳደር ሚናቸውን ዝቅ ማድረግ የተለመደ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ፤ ሴቶች ተስፋ ቆርጠው ወደ ኋላ መመለስ እንደሌለባቸው ገልጸዋል፡፡
ሴቶች የነገ ትውልድን የሚሰጡ፤ የቤተሰብ ምሰሶ እና ችግሮችን ቀድሞ መረዳት የሚችል ተፈጥሮ የታደሉ በመሆናቸው በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የመምራትና የመወሰን አቅማቸውን በተግባር የሚያሳዩበት እድል ሊፈጠርላቸው ይገባል ብለዋል፡፡
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሴት አባላት በተሰማሩበት ዘርፍ ውጤት በማስመዝገብ፤ የውክልና ስልጣን አምኖ ለሰጣቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ብቃታቸውን ማሳየት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
መንግስት የሴቶችን ተሳትፎ በተለያዩ ዘርፎች እያሳደገ መምጣቱን የገለጹት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ፤ ሴቶችም የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት፣ በተሰማሩበት መስክ ስኬታማና ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆን በራስ የመተማመን አቅማቸውን ሊያዳብሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
መንግስት የሴቶችን የመሪነት ሚና ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት ከዚህም በላይ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ነው ያሉት።
"ኢትዮጵያን ወክየ በተሰማራሁባቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ፈተናዎችን ተቋቁሜ በስኬት ተወጥቻለሁ" በማለት ልምዳቸውን ያካፈሉት ፕሬዝዳንቷ፤ ሴቶች ችግሮችን በመቋቋም የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ አደራ ብለዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ፤ የተመራጭ ሴቶች ኮከስ አባላት በምክር ቤቱ የተሰጣቸውን ህገ መንግስታዊ ኃላፊነት መወጣት እንዲችሉ በተለያየ ጊዜ የአቅም ግንባታ ስልጠና ይሰጣል ብለዋል፡፡
ሴት የምክር ቤት አባላት የሴቶችን ድምፅ ከፍ አድርጎ የማሰማት ድርብ ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ ወቅቱን የሚመጥን ዝግጅት ማድረግ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያን ለረጅም ዓመታት በአምባሳደርነት ያገለገሉት አምባሳደር ታደለች ኃይለሚካኤል በበኩላቸው፤ ሴቶች የተለየ ጥቅም ሳያስፈልጋቸው በራሳቸው አቅም ማደግና መለወጥ እንደሚችሉ መገንዘብ አለባቸው ብለዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ የሌሎችን ስኬታማ ሰዎች እውቀትና ልምድ መቅሰም፤ በውይይት ሀሳብ መለዋወጥና በንባብ አቅምን መገንባት እንደሚገባ በመጠቆም፡፡