በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሥርዓተ-ትምህርቱ አተገባበር፣ አሠራርና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሥርዓተ-ትምህርቱ አተገባበር፣ አሠራርና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ ተጠቆመ
አዲስ አበባ ሐምሌ 06/2015 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት በሥርዓተ-ትምህርቱ አተገባበር፣ አሠራርና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ አንድ ጥናት አመለከተ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተባባሪ አካላት ጋር በመሆን በትምህርት ጥራት ማሻሻያ ላይ ያዘጋጀው አውደ-ጥናት ምሁራንና የዘርፉ ባለሙያዎች በተገኙበት ተካሂዷል።
በእንግሊዝ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ለስድስት ዓመታት የተደረገው ጥናት የኢትዮጵያን የትምህርት ፖሊሲና የመማር ማስተማር ሂደቱን በስፋት የቃኘ መሆኑ ተገልጿል።
በጥናት ግኝቱ መሠረት ለኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት መጓደል አንደኛው ምክንያት የትምህርት አሰጣጡ የተማሪዎችን የክፍል ሽግግር እንጂ የእውቀት መሠረት የሌለው መሆኑ ተመላክቷል።
ለትምህርት ጥራት ማስጠበቂያ ሥራዎች ተብሎ የሚመደበውን በጀትም ለአስተዳደራዊ ሥራዎች የሚውል መሆኑ ሌላኛው ምክንያት ሆኖ ተነስቷል።
በትምህርት ሥርዓቱ የአሠራር ሥርዓትን ተከተሎ ያለመተግበርም ለትምህርት ሥርዓቱ መጓደል ሌላኛው ምክንያት ተደርጎ ተወስዷል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እና የጥናት ቡድኑ አባል ዶክተር በላይ ሐጎስ፤ ለኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት መጓደል በጥናቱ የተለያዩ ምክንያቶች መለየታቸውን ገልፀዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት በሥርዓተ-ትምህርቱ አተገባበር አሠራርና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ በጥናቱ ተመላክቷል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና፤ የኢትዮጵያ የትምህርት አሰጣጥ ከጥራት ይልቅ ተደራሽነት ላይ በማተኮሩ በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል ብለዋል።
በመሆኑም አሁን ላይ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ፖሊሲ ከማሻሻል ጀምሮ ሌሎችም ሥራዎች መከናወናቸው ለቀጣይ ጥሩ ተስፋ ያሳደረ መሆኑን ገልፀዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ፤ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መንግሥት የትምህርት ማሻሻያ የሪፎርም ሥራዎችን በስፋት ማከናወኑን ተናግረዋል።
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ጨምሮ በሌሎችም የአሠራር ማሻሻያ በማድረግ ለትምህርት ጥራት መጠበቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።