በክልሉ የሚስተዋለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት በልዩ ትኩረት ይሰራል-ዶክተር ይልቃል ከፋለ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሚስተዋለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት በልዩ ትኩረት ይሰራል-ዶክተር ይልቃል ከፋለ
ባህር ዳር ሐምሌ 6/2915 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በገጠርና በከተማ የሚስተዋለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፈለ ገለጹ።
በባህር ዳር ከተማ በ650 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ተጠናቆ ዛሬ ተመርቋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በክልሉ በሚገኙ ከተሞችና የገጠር አካባቢዎች መሰረታዊ ችግር እየሆነ መጥቷል።
የሰው ልጅ የኑሮ ደረጃ ከሚመዘንባቸው አንዱ የውሃ አቅርቦት መሆኑን ጠቁመው፣ ይህን መሰረታዊ ችግር ለመፍታት ክልሉ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የክልሉ መንግስት በሚመድበው በጀት እንዲሁም አጋር የልማት ድርጅቶችንና ህብረተሰቡን በማስተባበር የውሃ አቅርቦትን ለሁሉም ህብረተሰብ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።
ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋም በክልሉ የንፁህ መጠጥ ውሃን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተደረገ ላለው ጥረት አንድ ማሳያ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ይልቃል፣ ተደራሽነትን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩና የፌደራል ከፍተኛ አመራሮች በድን መሪ አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው የፌደራል መንግስት ለታላላቅ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የአስፋልት መንገዶች፣ የመስኖ ግንባታዎች፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች፣ የሃይል ማመንጫ ግድቦችና ሌሎች ፕሮጀክቶችን በመገንባት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
በዛሬው እለት የተመረቀው የባህር ዳር ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የፌደራል መንግስት ከጃፓን መንግስት ጋር ባለው መልካም ግንኙነት የተገነባ መሆኑን ገልፀዋል።
"የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት የህብረተሰቡን ጤንነት ለመጠበቅና ለኢኮኖሚ እድገት መሰረት ነው" ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ማማሩ አያሌው ናቸው።
በጃፓን መንግስት ድጋፍ በባህር ዳር ከተማ የአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ህዝብን ሙሉ ለሙሉ ተጠቃሚ የሚያደርግ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በ650 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ ለአገልግሎት መብቃቱን ተናግረዋል።
ሀላፊው እንዳሉት ፕሮጀክቱ 27 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የውሃ መስመር ዝርጋታ፣ ዘጠኝ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈር ወደ መስመር ማስገባት፣ የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከሮችና ሌሎች ግንባታዎችን አካቶ የተገነባ ነው።
"ፕሮጀክቱ ከ147 ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎችን ለ25 ዓመት ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን የከተማዋን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋንም ከ80 በመቶ በላይ ያደርሳል" ብለዋል።
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ በበኩላቸው የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የትምህርት፣ የግብርና፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና ሌሎች ልማቶችን እንደሚደግፍ ገልጸዋል።
ለዚህም ዛሬ የተመረቀው የባህር ዳር ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አንድ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው የውሃ ተቋሙ በጃፓን ኩባንያ የጥራት ደረጃውን ጠብቆ መገንባቱን ተናግረዋል።
የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ ሰብአዊነት በመሆኑ የጃፓን መንግስት በቀጣይም ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አመልክተዋል።
በንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ የምረቃ ሥነ ስርዓት ላይ የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ተገኝተዋል።