ቀጥታ፡

ዳያስፖራው ለጋራ ሀገራዊ ግብ መስራት እንደሚገባው የዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እንድሪስ ገለጹ

አዲስ አበባ ሐምሌ 6/2015(ኢዜአ):- ሀገር የሚገነበው ስኬትን በማስቀጠልና ጉድለትን እየሞሉ በመሄድ ስለሆነ ለጋራ ሀገራዊ ግብ በጋራ መስራት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እንድሪስ ገለጹ።

በካናዳ ኦታዋና አካባቢው ከሚኖሩ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና የቢዝነስ ዳያስፖራዎች፣ በተለያዩ የካናዳ መንግስታዊ ተቋማት ውስጥ ከሚሰሩ ባለሙያ ዳያስፖራዎችና የኮሚዩኒቲ ተወካዮች ጋር ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱም በዳያስፖራ ተሳትፎና ሀገራዊ ትስስር ዙሪያ በኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እንድሪስ የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በእስካሁኑ የዳያስፖራ ሁለንተናዊ ተሳትፎ አበረታች ውጤቶች መገኘታቸው ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

በውይይቱ ሀገራዊና ወቅታዊ አጀንዳዎች፣ የመረጃዎች ተደራሽነት ጉዳይ፣ የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግርንና የኢንቨስትመንት ተሳትፎን የማሳለጥ አስፈላጊነት ዙሪያ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

በተጨማሪም የኮንሱላርና የዳያስፖራ አገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታንና ተያያዥ ጉዳዮችን የተመለከቱ በርካታ ጥያቄዎችና ሀሳቦች ከዳያስፖራው ተነስተው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

በምላሹም ኢትዮጵያ በፈተና ውስጥ እያለፈች በርካታ ስኬት እያስመዘገበች እንደምትገኝ ተገልጿል።

ዳያስፖራው የመፍትሔ አካል በመሆን በሁኔታ ያልታጠረ የዳያስፖራ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባ ተነስቷል።

ሲንከባለሉ የመጡና ያደሩ የቤት ስራዎች ያሉባት ሀገር እንዳለችን ግንዛቤ በመውሰድ ሚዘናዊነትን፣ ተቀራርቦ መስራትንና መልካም ዕድሎችን ማስፋትን መርህ ያደረገ የዳያስፖራ ተሳትፎ ሊኖር ይገባል ተብሏል።

ተሳታፊ ዳያስፖራዎች በበኩላቸው ኢትዮጵያ እያጋጠሟት ካሉ ተግዳሮቶች አንጻር ያሏት ተስፋና ዕድሎች በርካታ መሆናቸውን እንደሚያምኑ ገልጸው፣ ጉድለታችንን እየሞላን እጅ ለእጅ ተያይዘን መጓዝ ይገባናል ብለዋል።

የውይይት መድረኩን ከዶክተር መሀመድ በተጨማሪ በካናዳ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፍጹም አረጋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ በላቸው ጉጅቦ መርተውታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም