አዳማ ከተማ የያዘችው የ'ስማርት ሲቲ' ፕሮጀክት እውን እንዲሆን የንግዱ ማህበረሰብ ተሳትፎውን ያጠናክራል -- ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
አዳማ ከተማ የያዘችው የ'ስማርት ሲቲ' ፕሮጀክት እውን እንዲሆን የንግዱ ማህበረሰብ ተሳትፎውን ያጠናክራል -- ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት
አዳማ ሐምሌ 06/2015 (ኢዜአ)፡- አዳማ ከተማ የያዘችው የ'ስማርት ሲቲ' ፕሮጀክት እውን እንዲሆን የንግዱ ማህበረሰብ ተሳትፎውን እንደሚያጠናክር የከተማው ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ገለፀ።
የአዳማ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት 50ኛ ዓመት ኤግዚቢሽንና ባዛርን ጨምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
የአዳማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ በየነ ቶሌራ እንደገለፁት የአዳማ 'ስማርት ሲቲ' ፕሮጀክትን እውን ለማድረግ ዘመናዊ የንግድ ስርዓት ማረጋገጥ ቀዳሚ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ምክር ቤቱ የንግዱ ማህበረሰብ በ'ስማርት ሲቲ' እሳቤ የተቃኘ እንዲሆንና በፕሮጀክቱ ውጤታማነት የድርሻውን ይወጣል ብለዋል።
በበዓሉ ምክንያት በሚካሄደው ኤግዝቢሽንና ባዛር አምራቾች፣ አስመጪዎችና አከፋፋዮችን ጨምሮ ከ500 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።
በዚህም የኢንዱስትሪ ምርቶች፣ የግብርናና ፋብሪካ ውጤቶች፣ የፍጆታ ዕቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ አምራቹንና ሻጩን ለማገናኘት ያለመ መሆኑን አመልክተዋል።
ኤግዚቢሽኑና በዛሩ ከነሐሴ 19 ጀምሮ እስከ ጷጉሜን 5 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ዝግጅቶች በአዳማ መስቀል አደባባይ ይካሄዳል ብለዋል።
ምክር ቤቱ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን ለማጠናከር፣ የከተማ ልማትና ዕድገትን ለማፋጠን በቀጣይ ይበልጥ ድርሻውን ይወጣል ብለዋል።