የኢትዮጵያና የሩስያን የቆየ ወዳጅነት በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው- በሩስያ የኢትዮጵያ አምባሳደር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና የሩስያን የቆየ ወዳጅነት በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው- በሩስያ የኢትዮጵያ አምባሳደር
አዲስ አበባ ሐምሌ 6/2015(ኢዜአ):- የኢትዮጵያና የሩስያን የቆየ ወዳጅነት በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በሩሲያ ፌዴሬሽን የኢፌዲሪ ልዩ መልእክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ቻም ኡጋላ ኡርያት ተናገሩ።
ኢትዮጵያና ሩስያ ከ125 ዓመታት በላይ የዘለቀ ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያላቸው ወዳጅ አገሮች መሆናቸው ይታወቃል።
በሩስያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ቻም ኡጋላ ኡርያት፤ የሀገራቱ የዲፕሎማሲ ግንኙነት በዘመናት ውጣ ውረድ ሳይዋዥቅ በአጋርነትና ትብብርን በማጠናከር እስካሁን የዘለቀ መሆኑን ተናግረዋል።
አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ተላቀው ነፃነታቸውን እንዲያገኙ በመደገፍ ሩስያ ታሪክ ሊዘነጋው የማይችል አቋም ይዛ የቀጠለች ሀገር መሆኗንም ጠቅሰዋል።
ከአድዋ ጦርነት ጀምሮ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷንና ነፃነቷን ለማስጠበቅ ያደረገችውን ትግል በመደገፍ ሩስያ ሁነኛ ወዳጅ መሆንዋን አምባሳደሩ ገልፀዋል።
የሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ ወዳጅነት ቀጥሎ ዛሬም በአካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ወጥ አጋርነት ይዘው መቀጠላቸውን አንስተዋል።
የጸጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ በዓለም አቀፍ መድረኮች ለኢትዮጵያ እውነታ በመቆምም አጋርነቷን ያሳየች ወዳጅ ሀገር መሆኗንም ተናግረዋል።
ሀገራቱ ካላቸው የረዥም ጊዜ ወዳጅነትና የዲፕሎማሲ ትብብር አንፃር የንግድ ትስስራቸው ብዙ መሻሻልን የሚጠይቅ ስለመሆኑ አምባሳደሩ ጠቁመዋል።
በተለይም በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በቱሪዝምና በቴክኖሎጂ መስኮች ትብብራቸውን ማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አምባሳደር ቻም ኡጋላ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሞስኮ የሚያደርገውን በሳምንት ሦስት ጊዜ በረራውን በቅርቡ ወደ አራት ማሳደጉን አስታውሰው፤ በቀጣይም የካርጎ አገልግሎት እንዲጀመር ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
በባህል ዲፕሎማሲ በኩልም በትምህርትና ሥልጠና ቀደም ሲል የነበረውን ትብብር ለማጎልበት የሁለቱ ሀገራት የትምህርት ተቋማት ትብብር እየተጠናከረ መሆኑን ገልፀዋል።
በወቅቱ ከ160 በላይ ኢትዮጵያውያን በሩስያ ነፃ ትምህርት ዕድል እየተማሩ ሲሆን፤ በትምህርት ተቋማት የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ለባህል ዲፕሎማሲ ለማዳበር በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከሩስያ ተጨማሪ ከቤላሩስ፣ አርመኒያ እና ሞልዶቫ ጋር የሚያጠናክሩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ለአብነትም በቤላሩስ የክብር ቆንስላ መሰየሙንና በሀገሪቱ ያሉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላትን ሀገራዊ ተሳትፎ በማሳደግ ጥሩ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።
አርመኒያም በአዲስ አበባ ኤምባሲ ለመክፈት ጥያቄ ማቅረቧን ጠቁመው፤ በሁለቱም አገራት መካከል የዲፕሎማሲ ሥራዎችን የማጠናከር ፍላጎት መኖሩን አምባሳደሩ ገልጸዋል።
ሩስያ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው፤ ከሳምንታት በኃላ በሩስያ በሚካሄደው የሩስያ-አፍሪካ ጉባዔም በዚህ ዙሪያ የላቀ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
አምባሳደር ቻም ኡጋላ ኡርያት፤ ተቀማጭነታቸው በሩስያ ሆኖ በአርመኒያ፣ ቤላሩስ እና ሞልዶቫ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።