በሮቤ ከተማ አስተዳደር እየተገነቡ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ለሌሎች ከተሞች ተሞክሮ የሚሆኑ ናቸው-- የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
በሮቤ ከተማ አስተዳደር እየተገነቡ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ለሌሎች ከተሞች ተሞክሮ የሚሆኑ ናቸው-- የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች
ሮቤ ሀምሌ 6/2015 (ኢዜአ) --በባሌ ሮቤ ከተማ አስተዳደር እየተገነቡ የሚገኙ ህብረተሰብ ተኮር የልማት ሥራዎች ለሌሎች ከተሞች መልካም ተሞክሮ የሚሆኑ መሆናቸውን የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።
በኦሮሚያ ክልል ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ከፌደራል መንግስት የመጡ የስራ ሀላፊዎች ቡድን በሮቤ ከተማ አስተዳደር እየተገነቡ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ጎብኝቷል።
በኃላፊዎቹ ከተጎበኙ የልማት ሥራዎች መካከል የከተማ ግብርና፣ የከተማ ማስዋብ ስራዎችና የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ይገኙበታል።
የፌደራል መንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከጉብኝቱ በኋላ እንዳሉት፣ በከተማዋ እየተሰሩ የሚገኙ ህብረተሰብ ተኮር የልማት ሥራዎች ለሌሎች ከተሞች መልካም ተሞክሮ የሚሆኑ ናቸው።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል የፌደራል ስነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነሩ ዶክተር ሳሙኤል ሁርቃቶ፣ በከተማዋ እየተሰሩ የሚገኙ የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት መንገድ ግንባታ፣ የአቅመ ደካማ ዜጎች ቤት እድሳት፣ የትምህርት ቤቶች ግንባታ በጥሩ ተሞክሮነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።
የልማት ሥራዎቹ የከተማዋን ነዋሪዎች የልማት ጥያቄዎች ተደራሽ ከማድረግ በተጓዳኝ በየአካባቢው ያሉ የልማት ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን መታዘብ ተችሏል ነው ያሉት።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ተሻለ በልሁ በበኩላቸው፣ የጉብኝቱ ዓላማ መንግስት ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድርግ የሚተገብራቸው አሰራሮች በምን አግባብ ተደራሽ እየሆኑ እንዳሉ ለማረጋገጥ ነው ብለዋል።
በሥራ ውስጥ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች የሚፈቱባቸው አቅጣጫዎች ላይ በየደረጃው ለሚገኙ የአካባቢው አመራሮች ድጋፍ ለማድረግ መሆኑንም አክለዋል።
አቶ ተሻለ እንዳሉት፣ በሮቤ ከተማ በህብረተሰቡ ተሳትፎ እየተሰሩ የሚገኙ የ'ቡኡረ ቦሩ' ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት፣ የአቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታ በምሳሌነት ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው።
የሌማት ትሩፋት አካል የሆነው የከተማ ግብርና ነዋሪው ባለው ውስን መሬት ላይ ከቤተሰብ ፍጆታነት አልፎ ተጨማሪ ገቢን በሚያስገኝ መልኩ እየተሰራበት መሆኑን በመስክ ምልከታቸው ማረጋገጣቸውን አንስተዋል።
''ከተማዋን አረንጓዴ ለማልበስና ለነዋሪዎቿ ምቹ የመኖሪያ ቦታ ለማድረግ እየተሰሩ የሚገኙ ሥራዎች በመልካምነት የሚጠቀሱ ናቸው'' ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ ናቸው።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒትስር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሀምሌ 10 ቀን 2015 ዓ ም በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ላቀረቡት አገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት እየተደረገ ያለው ዝግጅት በበጎ ጎኑ እንደሚጠቀስ አመልክተዋል።
የሮቤ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ሀሰን ሱልጣን በበኩላቸው፣ በከተማ አስተዳደሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ62 የሚበልጡ ፕሮጀክቶች ከ260 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቶቹ መንገድ፣ ትምህርት ቤት ግንባታና ጥገና፣ የመንገድ ዳር መብራት ዝርጋታ፣ ከተማ ውበትና አረንጓዴነት ላይ ያተኮሩ ናቸው።
አቶ ሀሰን እንዳሉት፣ የከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጉብኝት በሥራ ውስጥ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እንዲፈቱ አቅም ይፈጥራል።
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ በያን አብዳ በሰጡት አስተያየት፣ በከተማ አስተዳደሩ የህብረተሰቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄን መሰረት በማድረግ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ በመሆናቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሰሞኑን የፌደራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ከሀምሌ 1 እስከ 10 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ወደ ክልሎች በመንቀሳቀስ ድጋፍና ክትትል እንደሚያካሄዱ ማሳወቃቸው ይታወሳል።