ቀጥታ፡

የፍየል ዝርያ ማሻሻል ሥራ ውጤታማ እያደረገን ነው -የሳላማጎ ወረዳ አርብቶ አደሮች

ጂንካ ሐምሌ 6/2015 (ኢዜአ) በቆላማ አካባቢ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አማካይነት በሙከራ ደረጃ የጀመሩት የፍየል ዝርያ ማሻሻል ሥራ ውጤታማ እያደረጋቸው መሆኑን በደቡብ ኦሞ ዞን የሳላማጎ ወረዳ አርብቶ አደሮች ተናገሩ። 

ፕሮጀክቱ ከእንስሳት ሀብት ከቁጥር ይልቅ፤ ጥራት ላይ መሠረት በማድረግ የአርብቶ አደሩ የኑሮ መሠረት የሆነው የእንስሳት እርባታ ለማዘመን በወረዳው ሹሙቶን ጨምሮ በሁለት ቀበሌዎች የፍየል ዝርያ ማሻሻያ እያከናወነ ይገኛል።

 

ጥሩ ቁመና ያላቸውን ፍየሎች ከአካባቢው ዝርያ በመምረጥና በማዳቀል ምርታማነታቸውን በእጥፍ ለማሳደግ እየተከናወነ ያለው ሥራ ውጤታማ መሆኑን የአካባቢው አርብቶ አደሮች ተናግረዋል።

በሥራው ተጠቃሚ ከሆኑ የአካባቢው አርብቶ አደሮች መካከል አቶ ተረፈ ታሎ በአካባቢያቸው የእንስሳት ቁጥርን መሠረት አድርገው የሚያካሂዱ የእንስሳት እርባታ ኑሮአቸውን እንዳልቀየረው ገልጸዋል።


 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቆላማ አካባቢ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት በተደረገላቸው የክህሎት ስልጠናና የገንዘብ ድጋፍ የጀመሩት የፍየል ዝርያ የማሻሻል ሥራ ውጤታማ እያደረጋቸው መሆኑን አመልክተዋል።

ያልተዳቀሉ ፍየሎችን አርብተው ለገበያ በማቅረብ የቆየ ልምድ እንዳላቸው የተናገሩት አርብቶ አደር ተረፈ፣ አሁን እያካሄዱ ያሉት የተዳቀሉ ፍየሎች እርባታ አዋጪ መሆኑን ተናግረዋል።

ፍየሎቹ በአጭር ጊዜ ለገበያ የሚደርሱ ከመሆናቸውም በላይ፤ ዋጋቸውም ከሌሎች ፍየሎች ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ እንደሚጨምር አመልክተዋል።

ሌላኛዋ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ አርብቶ አደር ካጩራ ካዲዱ ከ12 ሴቶች ጋር በመሆን በቡድን በመደራጀት የጀመሩት የፍየል ማዳቀል ሥራ ውጤት እያስገኘላቸው መሆኑን ገልጸዋል


 

ቀደም ሲል አንድ ፍየል አድጎ ለገበያ እስኪቀርብ ከአራት እስከ አምስት ዓመት እንደሚፈጅ ገልጸው፣ "አሁን ከአካባቢው የተሻሉ ዝርያዎችን በመምረጥና በማዳቀል በአንድ ዓመት ውስጥ ለገበያ ይቀርባሉ፤ የተሻለ ዋጋም ያወጣሉ" ብለዋል።

በፕሮጀክቱ በተሰጣቸው ሰባት የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው ፍየሎች ድጋፍ የጀመሩት የማዳቀል ሥራ አሁን ከ70 የሚበልጡ ፍየሎች ባለቤት አንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

በተጨማሪም ቡድኑ የገንዘብ ቁጠባ መጀመሩንና በቀጣይም ሥራውን በማስፋፋት በይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን እየሰራ መሆኑን አርብቶ አደር ካጩራ አስታውቀዋል።


 

የሳላማጎ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊና የእንስሳትና አሳ ሀብት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ወንድወሰን ተፈራ ከቆላማ አካባቢ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ጋር በመሆን በወረዳው ሁለት ቀበሌዎች የተጀመረው ማህበረሰብ አቀፍ የፍየል ዝርያ ማሻሻል ሥራ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል ።

በአካባቢው በተመረጡና የተሻለ ቁመና ባላቸው ፍየሎች በተጀመረው የማዳቀል ስራ 348 ግልገሎች እንዳስገኘ ተናግረዋል። "ይህም በአካባቢው ያለውን የፍየል ምርታማነት በእጥፍ ያሳድጓል " ብለዋል።

በቀጣይም በተመረጡ ፍየሎች የተጀመረው የማዳቀል ሥራ በማስፋፋትና ለአካባቢው የተሻሻለ የፍየል ዝርያ የዘረ-መል ምንጭ በማድረግ አርብቶ አደሩ ተጨማሪ ጥቅም እንዲያገኝ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በደቡብ ኦሞ ዞን አርብቶ አደር ጉዳይ መምሪያ የቆላማ አካባቢ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አፊሰር ዶክተር ኢብራሂም ገብረ መስቀል ዞኑ በፍየል እርባታ በደቡብ ክልል በአንደኛ ደረጃ ላይ ቢቀመጥም፤ እርባታው ብዛትን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በፕሮጀክቱ የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በብዛት ላይ የተመሰረተውን ባህላዊ የእርባታ ዘዴ ለማዘመን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የፍየል ዝርያ ማሻሻል ሥራም የፕሮጀክቱ አካል እንደሆነ አስረድተዋል።

ፕሮጀክቱ የፍየል ዝርያ ማሻሻል ሥራውን በዞኑ በሚገኙ በስድስት አርብቶ አደር ወረዳዎች ተግባራዊ በማድረግ ላይ  እንደሚገኝ የገለጹት ዶክተር ኢብራሂም፤"በነዚህ ወረዳዎች ከአካባቢው ዝርያ በተመረጡ 210 ፍየሎች የተጀመረው የማዳቀል ስራ  550 ግልገሎች አስገኝቷል" ብለዋል።

የተሻሻሉና የተዳቀሉ የፍየል ዝርያዎች ካልተዳቀሉት ጋር ሲነፃፀሩ ምርታማነታቸው በእጥፍ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።

በዞኑ ከፕሮጀክቱ በተጨማሪ ዘንድሮ ዳልጋ ከብቶች በሰው ሰራሽና በኮርማ በማዳቀል 1 ሺህ 500 የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ጥጃዎች መወለዳቸውም የዞኑ ግብርና መምሪያ መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም