ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እና የኬንያ ሁለንተናዊ ግንኙነት እንዲጠናከር እየተሰራ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ሐምሌ 5/2015 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ እና የኬንያ ሁለንተናዊ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር እየተሰራ እንደሚገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

አቶ ደመቀ በናይሮቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተዘጋጀ ስነ-ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ሁለቱ አገሮች ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ልማት በጋራ ይሰራሉ ብለዋል።

የአገራቱ ሁለንተናዊ ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

የኤምባሲው አመራር እና መላው ሰራተኞች ለግንኙነቱ መጎልበት ጠንክረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌ የኤምባሲው አባላት የተሰጣቸውን የመንግስት እና የሕዝብ ተልዕኮ ለመወጣት በትጋት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ኤምባሲውን በመጎብኘታቸው አመስግነዋል።

አቶ ደመቀ መኮንን ነገ በሚጀመረው 43ተኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ለመሳተፍ ኬንያ መግባታቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም