ቀጥታ፡

አዲስ አበባ ሰላሟ እንዲጠበቅ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር ወሳኝነት አለው - ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ


አዲስ አበባ ሐምሌ 5/2015 (ኢዜአ):-አዲስ አበባ ሰላሟ እንዲጠበቅ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር አስፈላጊ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች በሰላምና ደህንነት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርገዋል።

May be an image of 9 people

ውይይቱ የተደረገው ከመንግስትና ከግል ባንኮች እንዲሁም ከጥበቃ ኤጀንሲ ኃላፊዎች ጋር ነው።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ አዲስ አበባ ሰላሟ እንዲጠበቅ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የግል ጥበቃ ኤጀንሲዎች መጠናከርና መደራጀት የሕዝብና የመንግስት ንብረት ከመጠበቅ ባለፈ የከተማዋ ሰላም የተረጋጋ እንዲሆን ከማስቻል አንጻር አጋዥ ሚና እንዳላቸው አመልክተዋል።
ይሁንና አንዳንድ የጥበቃ ኤጀንሲዎች ከምልመላ፣ ከስልጠና፣ ከስምሪት እና ከክትትል መጓደል የተነሳ የፀጥታ ችግር እየፈጠሩ እንዳሉ አንስተዋል። 

ኤጀንሲዎች ማንነታቸውን ሳያጣሩ በሚቀጥሯቸው የጥበቃ ሰራተኞች አማካኝነት በባንኮች እና በተቋማት ላይ የሚፈፀም ዝርፊያ፣ ሌብነት እና ሌሎች ወንጀሎች እየተፈጸሙ መሆኑን ነው ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ ያመለከቱት።

የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን ለማስተካከል የተወሰዱ እርምጃ ቢኖሩም በቀጣይም ሁኔታዎች እየተሻሻሉ የማይመጡ ከሆነ ጠንከር ያለ የማስተካከያ እርምጃዎች እንደሚወሰድ እና በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስገንዝበዋል።

የፖሊስ ተቋማት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተጣምሮ መስራት አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው ማንነታቸው ሳይጣራ የተቀጠሩ የጥበቃ ሰራተኞች ከግለሰብ ደረጃም አልፈው በቡድን በመደራጀት ከፀረ-ሰላም ኃይሎች ተልዕኮ በመውሰድ ለጥበቃ ስራ በታጠቁት የጦር መሳሪያ በማስፈራራት ለመጠበቅ የተቀጠሩበትን ተቋም በመዝረፍ እና የተሰጣቸውን የጦር መሳሪያ ይዘው የሚሰወሩ እንዳሉ ገልጸዋል።

በውይይት ላይ በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋሉ ወንጀሎችን የሚዳስስና የወንጀል አዝማሚያዎችን ያመላከተ የመወያያ ሰነድ ቀርቦ ውይይት የተደረገ ሲሆን ከባለድርሻ አላት ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም