በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የተከናወኑ የልማት ስራዎች የሚያበረታቱና የብልፅግና ጉዞ ስኬት ማሳያ ናቸው-ከፍተኛ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የተከናወኑ የልማት ስራዎች የሚያበረታቱና የብልፅግና ጉዞ ስኬት ማሳያ ናቸው-ከፍተኛ አመራሮች
ቦንጋ ሐምሌ 5 ቀን 2015(ኢዜአ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የተመለከቷቸው የልማት ስራዎች የሚያበረታቱና ለተጀመረው የብልፅግና ጉዞ መሳካት ማሳያ መሆናቸውን ወደ ክልሉ የተሰማሩት የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በገለጹት መሠረት የፌዴራል መንግስት የሥራ ኃላፊዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ድጋፍና ክትትል እያደረጉ ነው።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በተመሳሳይ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
የፌዴራል መንግስት የሥራ ኃላፊዎቹ በክልሉ ሸካና ቤንች ሸኮ ዞኖች በአረንጓዴ አሻራ ልማት በመሳተፍ የክረምት በጎ ፈቃድ ስራዎችን አስጀምረዋል።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ የድጋፍና ክትትሉ ዓላማ በየዘርፉ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን መገምገም መስተካከል ያለባቸውን ደግፎ እንዲስተካከል ማድረግ ነው ብለዋል።
እንዲሁም ልምድ ሊወሰድባቸው የሚገቡ የልማት ስራዎችን ልምድ ለመቅሰም መሆኑንም ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
በክልሉ በሸካና በቤንች ሸኮ ዞኖች የተመለከቱት የልማትና የፀጥታ ሁኔታ ተስፋ ሰጪና የሚበረታታ መሆኑን ዶክተር ዓለሙ ገልጸዋል።
በዞኑቹ የተመለከቷቸው የሌማት ትሩፋትን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ስራዎችና ሌሎች ግንባታዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳህረላህ አብዱላሂ በበኩላቸው በዞኖቹ በጣም ሰፋፊ የልማት ስራዎች እየተካሄዱ መሆናቸው እንደተመለከቱ አስታውቀዋል።
በአረንጓዴ አሻራ የሚደረገው እንቅስቃሴና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማሩ የአረጋዊያን ቤቶች ግንባታ፣ የሌማት ትሩፋት ስራዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን ማረጋገጥ የቻልንበት ጉብኝት ነው ብለዋል።
በቅመማቅመም፣ ቡናና ሌሎች ከአካባቢው አልፎ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ምርቶች በሰፊው የሚመረትበት አካባቢ መሆኑን እንደተመለከቱም ወይዘሮ ሳህረላህ ተናግረዋል።
ከፍተኛ አመራሮቹ በቤንች ሸካ ዞን በጉራፈርዳ ወረዳ በኩታ ገጠም የለማ የበቆሎና የሩዝ ልማት፣ የኩጃ ወር ብዜት እርሻ፣ የኤስቡም አግሮ ኢንዱስትሪ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የስራ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል።
በተጨማሪም፣ የበበቃ እርሻ ልማት፣ የሚዛን አማን አለም አቀፍ አየር ማረፊያ የግንባታ የተመለከቱ ሲሆን፣ የአረጋዊያን መኖሪያ ቤት ግንባታንም አስጀምረዋል።
በጉብኝቱም የአካባቢው የመንግስት የስራ ሀላፊዎችም ተገኝተዋል።