በደቡብ ወሎ ዞን የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በቅንጅት እየተደረገ ያለውን ጥረት እናግዛለን--የአመራሮች ቡድን - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ወሎ ዞን የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በቅንጅት እየተደረገ ያለውን ጥረት እናግዛለን--የአመራሮች ቡድን
ደሴ ሐምሌ 5/2015(ኢዜአ)፦ በደቡብ ወሎ ዞን የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል አመራሩ ከህብረተሰቡ ጋር እያደረገ ያለውን ጥረት በማገዝ የበኩሉን እንደሚወጣ በዞኑ ድጋፍና ክትትል እያደረገ ያለው የፌደራል ቡድን ገለፀ።
የፌደራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተዘዋውረው የተከናወኑ ልማቶችን በመመልክትና በመደገፍ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተሰጠ መምሪያ መሰረት አመራሮቹ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው ድጋፍና ክተትል እያደረጉ ነው።
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሜቴ አባልና በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስተባባሪ አምባሳደር ሐሰን አብዱልቃድር የተመራ ቡድን ዛሬ በደቡብ ወሎ ቃሉ ወረዳ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በመመልከት የአንድ ትምህርት ቤት ግንባታ ሥራን አስጀምሯል።
አምባሳደሩ በእዚህ ወቅት እንዳሉት የክረምት የልማት ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑና ያረጁና ከደረጃ በታች የሆኑ ትምህርት ቤቶችን ለማሻሻል የተጀመሩ ስራዎችን የማጠናከር ሥራ ቡድኑ እያከናወነ ይገኛል።
በዚህም በደቡብ ወሎ ዞን ከደረጃ በታች ያሉ ትምህርት ቤቶችን ደረጃና ገጽታ ለማሻሻል አመራሩ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ እያከናወነ ያለው ሥራ የሚደነቅ መሆኑንና ለማጠናከርም ቡድኑ የድርሻውን ይወጣል ብለዋል።
"በርካታ ትምህርት ቤቶች ለ2016 የትምህርት ዘመን ምቹና የተሻሉ እንዲሆኑ በምንችለው አቅም ሁሉ እንደግፋለን፣ ለዘላቂነታቸውም በፌዴራል መንግስት ጭምር ትኩረት እንዲያገኙ ይደረጋል" ሲሉም አክለዋል።
ባለሃብቱና ህብረተሰቡም የጀመረውን ሁለንተናዊ የልማት ተሳትፎ በማጠናከር የትምህርቱን ዘርፍ በማሳደግ ብቁ፣ አምራችና የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት መረባረብ እንዳለበትም አምባሳደር ሐሰን አሳስበዋል።
በተለይ ባለሀብቱ "ትምህርት ለትውልድ" በሚል ልዩ ዘመቻ ወደ ተማሩበት ትምህርት ቤትና ወደ አካባቢያቸው በመሄድ ለትምህርት ቤቶች መሻሻል ጉለህ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን በበኩላቸው እንዳሉት በዞኑ ከደረጃ በታች የሆኑ ትምህርት ቤቶችን ለማሻሻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
ይህን ጅምር ስራ ከማጠናከር ባሻገር ከአቅም በላይ የሆኑ ክፍተቶች በፌዴራል መንግስት እንዲሸፈኑ የቡድኑ መምጣት ወሳኝ መሆኑን ነው የተናገሩት።
"ትምህርት ለትውልድ" በሚል መርህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባስጀመሩት ንቅናቄ ባለሃብቱንና የአካባቢውን ተወላጆች በማስተባበር እየሰራን ነው'' ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደረጀ አማረ ናቸው።
ለዚህም በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ "ሩጋዝ" የኤሌክትሮኒክስ አማራች ድርጅት በቃሉ ወረዳ በ4 ሚሊዮን ብር የሚያስገነባው የኮረብቲት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።
ሌሎች የትምህርት ቤት ማሻሻያ ሥራዎችም በክረምቱ እንደሚከናወኑ ጠቁመው፤ "በርካታ ትምህርት ቤቶችን በማሻሻል በ2016 የትምህርት ዘመን ምቹ ለማድረግ እንረባረባለን" ብለዋል።
በዞኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የ162 ትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ሥራ እየተከናወነ ነው።
የሩጋዝ ኤሌክትሮኒክስ አምራች ድርጅት ተወካይ አቶ ኡመር ብርቁ በበኩላቸው፣ "የዞኑ ትምህርት መምሪያ ባደረገንል ጥሪ መሰረት በአካባቢያችን ከደረጃ በታች ያሉ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የድርሻችንን እንወጣለን" ብለዋል።
ከፌዴራል መንግስት ወደ ደቡብ ወሎ ዞን ያቀናው የከፍተኛ አመራር ቡድን በአርጎባ ወረዳ የተለያዩ ልማቶችን ከተመለከተ በኋላ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራውን ማኖሩ ይታወሳል።