ቀጥታ፡

በጋሞ ዞን እየተካሄደ ያለው የልማት እንቅስቃሴ አበረታች ነው- የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች

አርባ ምንጭ ሐምሌ 05/2015 (ኢዜአ) በጋሞ ዞን እየተከናወነ ያለው አበረታች የልማት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ። 

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለ10 ቀናት ወደ ክልሎች በመሄድ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉ መግለጻቸው ይታወሳል።

በዚሁ መነሻነት የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ቡድኑ ባለፉት ሁለት ቀናት በዞኑ የጨንቻና አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳዎች  የልማት እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል።

በአርባ ምንጭ ከተማ ዜጎች በማህበር ተደራጅተው የሚያከናውኗቸውን የዶሮ፣ ዓሣና የወተት ላሞች ልማት እንቅስቃሴን ተመልክተዋል።

በተጨማሪም በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ የሆነውን የአርባ ምንጭ ሲቀላ መሰናዶና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም የዶክተር አመኑ መታሰቢያ ሆስፒታልን ጎብኝተዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ ለኢዜአ እንዳስታወቁት የጉብኝቱ ዓላማ መንግስት የነደፋቸው የልማት ፕሮግራሞች በተዋረድ ምን ያህል እየተፈጸሙ እንደሚገኙ ለማወቅና ምርጥ ተሞክሮ ከክልሎች ለመቀመር ነው።

አመራሮቹ የአካባቢውን የልማት እንቅስቃሴ መጎብኘታቸው በየደረጃው ያለው አመራርና ሕዝቡ በልማቱ የበለጠ እንዲተጋ ማነሳሳቱን ገልጸዋል።

የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ከተነደፉት ግቦች መካከል በወተት ምርትና ዶሮ እርባታ አበረታች ሥራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በዓሣ ልማት ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ ይህ ውጤታማ እንቅስቃሴ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ዶክተር ፍቅሩ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማሪዮ በበኩላቸው በዞኑ በግብርናው ዘርፍ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ከፍተኛ አቅም መኖሩን መመልከታቸውን ገልጸዋል።

በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም በእንስሳት ሀብት አርሶ አደሩ ተሰማርቶ ተጠቃሚ መሆን የጀመረባቸው መስኮች ለሌሎች አካባቢዎች ተሞክሮ የሚሆን ነው ብለዋል።

የፌዴራል አስፈጻሚ አካላት አመራሮች አካባቢውን መጎብኘታቸው የልማት እንቅስቃሴውን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከፍተኛ አቅምና መነሳሳት ይፈጥራል ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡት ደግሞ የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቃፌ ቃፍሬ ናቸው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም