በትግራይ ክልል ከስደት ለተመለሱ ወጣቶች የሥራ መሳሪያዎች ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል ከስደት ለተመለሱ ወጣቶች የሥራ መሳሪያዎች ድጋፍ ተደረገ

መቀሌ ሓምሌ 5 /2015 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል ከስደት ለተመለሱ ወጣቶች ራሳቸውን የሚችሉበት 1 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የሥራ መሳሪያዎች ድጋፍ መደረጉን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ይሄይሽ ስባጋድስ ለኢዜአ እንደገለፁት የመስሪያ ማሽኖች ድጋፍ የተደረገው ከስደት ለተመለሱ 13 ወጣቶች ነው።
ድጋፉ የልብስ ስፌትና ጥልፍ ሥራ እንዲሁም ለፀጉር ማስተካከያ የሚያገለግሉ ማሽኖች ያካተተ መሆኑንም ተናግረዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ ድጋፉን ያደረጉት የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) ብራይት ስታር ሪሊፍ ኤንድ ዲቨሎፕመንት ከተሰኘ መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር ነው።
የሥራ መስሪያዎቹ ድጋፍ የተደረገላቸው ወጣቶች በመረጡት ሙያ በድርጅቱ ስልጠና እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።
'የብራይት ስታር ሪሊፍ ኤንድ ዲቨሎፕመንት' ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግዛቸው አይካ በበኩላቸው፣ ወጣቶቹ ህይወታቸውን እንዲለውጡ የሙያ ስልጠና በድርጅቱ እንደተሰጣቸው አረጋግጠዋል።
ወጣቶቹ በሚፈልጉት ሙያ በምርጫቸው ለሚሰሩት ስራ የሚያገለግሉ የሥራ መሳሪያዎች እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል።
ድጋፉ ከተደረገላቸው ወጣቶች መካከል ወጣት መሰለ ወልደሰንበት በ2013 ዓ.ም ወደ ሳኡዲ ዓረቢያ በመሄድ እዛም ብዙ መከራ ማሳለፉን ይገልጻል።
ወጣቱ አሁን ያገኘውን እድል ተጠቅሞ ሰርቶ ለመለወጥ ዝግጁ መሆኑን ገልጾ፤ ለድጋፍም ምስጋና አቅርቧል።