የሩሲያ - አፍሪካ የኢኮኖሚና ሰብዓዊነት ፎረም በትብብር ላይ የተመሰረተና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋገጥ ነው - አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን - ኢዜአ አማርኛ
የሩሲያ - አፍሪካ የኢኮኖሚና ሰብዓዊነት ፎረም በትብብር ላይ የተመሰረተና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋገጥ ነው - አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን
አዲስ አበባ ሐምሌ 5/2015(ኢዜአ)፦ የሩሲያ - አፍሪካ የኢኮኖሚና ሰብዓዊነት ፎረም በትብብር ላይ የተመሰረተና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋገጥ መሆኑን በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ገለጹ፡፡
በሩሲያ ሴንት ፒተርስበርግ ከተማ እ.ኤ.አ ከሐምሌ 27-28/2023 የሚካሄውን ሁለተኛው የሩሲያ-አፍሪካ የኢኮኖሚና ሰብዓዊነት ፎረምን በማስመልከት በአዲስ አበባ ውይይት ተደርጓል፡፡
በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አባላት እና የሩሲያ የንግድና ኢንዱስትሪ ልዑካን ቡድን ተሳትፈዋል፡፡
የአፍሪካን እና የሩሲያን በትብብር ላይ የተመሰረተ እድገት ማፋጠንን ዓላማ ያደረገውና የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ አካል የሆነው የኢኮኖሚና የሰብዓዊነት ፎረም ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው በፈረንጆቹ 2019 በሩሲያ ሶቺ ከተማ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን፤ የሩሲያ-አፍሪካ ግንኙነት አሁን ባለው የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ብዙ ጫናዎች ቢኖሩበትም ትብብሩ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የሩሲያና አፍሪካ የኢኮኖሚና የሰብዓዊነት ፎረም በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በፖለቲካ፣ በደህንነት፣ በባህልና በሰብዓዊ ድጋፎች ዙሪያ በጋራና በትብብር ለመስራት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፎረሙ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ጠንካራ ትብብር በመመስረት አፍሪካን የንግድ ማዕከል ማድረግ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ሁሉን አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ለማሳደግ ፎረሙ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ከቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የተላቀቀ የትብብር መንፈስ መገንባት እንደሚገባ በማንሳት ፎረሙ ለዚህ ስኬት ትልቅ ሚና እንዳለው አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው፤ የሩሲያ አፍሪካ ኢኮኖሚና ሰብዓዊነት ፎረም ምርትና አገልግሎትን ከመሸጥም በላይ የቴክኖሎጂና እውቅት ሽግግር ይፈጥራል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያና ሩሲያ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጎልበት የዘርፉ ተዋንያን ያላቸውን ጸጋ በአግባቡ እንዲጠቀሙ ያግዛል ነው ያሉት፡፡
የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳለጥና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሩሲያ ኩባንያዎች ትልቅ አቅም እንደሚፈጥሩም ጠቁመዋል፡፡
በሩሲያ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ትብብር ኮሚቴ ሊቀ-መንበር ኢጎር ሞሮዞቭ የንግድና ኢንቨስትመንት አቅጣጫችንን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ወደሚገኝባት አፍሪካ አዙረናል ብለዋል፡፡
ሩሲያ በዓለም አቀፍ ጫናዎች ውስጥ ሆና የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም በጥራጥሬ እህልና የአፈር ማዳበሪያ ምርት ከዓለም ቀዳሚ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
አፍሪካውያን ያላቸውን አቅም በአግባቡ ተጠቅመው ሰላማቸውንና የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ እንዲችሉ የሩሲያ ኩባንያዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡