የትምህርት ተቋማት የሚያስፈልጓቸውን ግብዓት ለማሟላት የሚደረገውን ጥረት ሕብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ተቋማት የሚያስፈልጓቸውን ግብዓት ለማሟላት የሚደረገውን ጥረት ሕብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ
አዲስ አበባ ሐምሌ 05/2015 (ኢዜአ) የትምህርት ተቋማት የሚያስፈልጓቸውን ግብዓት በማሟላት ደረጃቸውን የጠበቁ ለማድረግ ሕብረተሰቡ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያጠናክር የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጥሪ አቀረበ።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከወላጅ የተማሪ ሕብረት፣ ከትምህርት አመራሮችና ከመምህራን ማኅበር ጋር የትምህርት ተቋማትን ደረጃ ማሻሻልን የተመለከተ ውይይት አካሂዷል።
በአዲስ አበባ 567 ቅድመ መደበኛ፣ የመጀመሪያና ሁለተኛ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ የትምህርት ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አራት ትምህርት ቤቶች በዝቅተኛ ደረጃ፤ 238 ትምህርት ቤቶች ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
እነዚህ ትምህርት ቤቶችም ደረጃቸውን ያልጠበቁ የመማሪያ ክፍሎች፣ የላቦራቶሪና ቤተ-መጽሐፍት ያሉባቸው መሆኑ ተጠቅሷል።
ይህንንም ተከትሎ ትምህርት ቤቶች የሚያስፈልጓቸውን ግብዓቶች በሟሟላት ወደ ደረጃ ሦስትና አራት ለማሸጋገር እየተሰራ ነው።
በዚህም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ትኩረት መደረጉን ነው ቢሮው የገለፀው።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የትምህርት ተቋማት ደረጃቸውን እንዲጠብቁ ሁላችንም ኃላፊነት አለበት ብለዋል።
ጠንካራ አገር የሚገነባው በተማረ የሰው ኃይል መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህ ደግሞ የትምህርት ጥራትን የሚያረጋግጥ የትምህርት ተቋም ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ይህንንም ከግምት በማስገባት ደረጃውን በጠበቀ የትምህርት ተቋም ተማሪዎች በዕውቀት፣ ክህሎት እና ሥነ-ምግባር ታንፀው እንዲወጡ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህንንም እውን ለማድረግ በተለይም ሕብረተሰቡ በመዲናዋ የሚገኙ የትምህርት ተቋማትን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በቢሮው ምክትል ኃላፊ የሆኑት ወንድሙ ዑመር በበኩላቸው፤ የትምህርት ተቋማት ያሉባቸውን ችግሮች የመለየት ሥራ መሠራቱን ገልፀዋል።
በትምህርት ቤቶች የተማሪ ክፍል ጥምርታውን ለማስተካከል ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችና ሌሎች ግብዓቶች እየተሟሉ መሆኑን ተናግረዋል።
በውይይቱ የተሳተፉት በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ 2 ሕዝባዊ ሠራዊት የቅድመና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ-መምህር ቢኒያም ተሾመ በበኩላቸው፤ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል እየተካሄደ ያለው ንቅናቄ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
በተለይም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል እየተደረገ ያለውን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም ሕብረተሰብ በአካባቢው ያሉ ትምህርት ቤቶችን ማገዝ አለበት ብለዋል።