ቀጥታ፡

በደቡብ ወሎ ዞን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን አረጋግጠናል- ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን አባላት 

ደሴ ሐምሌ 5/2015 (ኢዜአ)  በደቡብ ወሎ ዞን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ባደረጉት ምልከታ ማረጋገጣቸውን ክትትልና ድጋፍ እየሰጡ ያሉ የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን አባላት ገለፁ።

በብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሜቴ አባልና በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስተባባሪ አምባሳደር ሐሰን አብዱልቃድር የተመራ ልዑክ በደቡብ ወሎ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የመስክ ምልከታ አድርጓል።

አባላቱ በምልከታቸው በአካባቢው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ህዝብን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን መመልከታቸውን ገልፀዋል።

የልዑካን ቡድኑ አስተባባሪ አምባሳደር ሐሰን አብዱልቃድር እንዳሉት በዞኑ አርጎባ ብሔረሰብ፣ ቃሉና ተሁለደሬ ወረዳዎች የተከናወኑ የተለያዩ የልማት ሥራዎችንና የክረምት ተግባራት ቅደመ ዝግጅቶችን ተመልክተዋል፡፡
በዚህም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ አድርገናል በሚል በአመራር የቀረበን ሪፖርት በተግባር ማረጋገጥ መቻላቸውን ነው የገለጹት።

በመስክ ጉብኝት ወቅት የተፈጥሮ ሀብት ሥራ፣ የሌማት ቱርፋት፣ የቆላ ፍራፍሬ ልማት፣ የትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻል፣ የኢንቨስትምንት እንቅስቃሴ፣ የክረምት በጎ ፍቃድና ችግኝ ተከላ ቅደመ ዝግጅትና ሌሎችንም መመልክታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ለሌሎች አካባቢዎች ጭምር ምሳሌ የሚሆኑ የልማት ተግባራትን ማየታቸውን የተናገሩት አምባሳደር ሐሰን፤ በልማት ሥራዎቹ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ መሆኑንም ገልጸዋል።

በውሃ አቅርቦት እና የገበያ ትስስር በመፍጠር በኩል ያለው ክፍተት መስተካከል እንዳለበትም አመልክተዋል።

በወረዳ፣ በዞንና በክልል ደረጃ ሊፈቱ የሚችሉት እንዲፈቱ አቅጣጫ መሰጠቱን ጠቅሰው፤ "በፌደራል መንግስት የሚፈቱትን ደግሞ ለሚመለከተው አካል በማድረስ እንዲፈቱ በልዑክ ቡድኑ በኩል ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል" ብለዋል።

የህብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ጌታቸው መለሰ በበኩላቸው እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የሰጡትን መመሪያ መሰረት በማድረግ በደቡብ ወሎ ዞን የተከናወኑ የልማት ሥራዎችና የክረምት ተግባራት ቅደመ ዝግጅትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ቀደም ሲል በአመራር ለአመራር ውይይት ተከናውነዋል ተብለው በሪፖርት የተገለጹ የልማት ሥራዎች ተጨባጭ ስለመሆናቸው በድጋፍና ክትትል ወቅት ማረጋገጣቸውን ጠቅሰው፤"በምልከታ የተለዩ ክፍተቶች በቀጣይ እንዲስተካከሉ እንደ አመራር ድጋፍና ክትትል እናደርጋለን" ብለዋል።

በተለይ የቆላ አትክልትና ፍራፍሬ በአካባቢው በብዛት ቢመረትም በገበያ ትስስር ችግር ምክንያት አርሶ አደሩ በልፋቱ ልክ መጠቀም እንዳልቻለ ማየታቸውን ጠቅሰው፣ በቅርቡ የገበያ ትስስር ለመፍጠር በመንግስት በኩል እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

አርሶ አደሮች በብዙ ልፍትና ድካም ያመረቱትን ምርት በተሻለ ሸጠው የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑየ ከተለያዩ ክልሎች ጋር የገበያ ትስስር መፍጠር እንደሚቻልም ገልጸዋል።

"በዞኑ የተመለከትነው የልማት ሥራና የህብረተሰቡ ተሳትፎ የሚደነቅና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው" ያሉት ደግሞ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ናቸው።

በውሃ አቅርቦትና በሌሎችም የሚስተዋሉ ጥቃቅን ክፍተቶችን በቅንጅት ለመሙላት እንደሚሰራም አመልክተዋል።

የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ቀጣይ በደሴና በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደሮችም ተመሳሳይ ምልከታ አድርገው አቅጣጫ እንደሚያስቀምጡም ከተገኘው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም