ቀጥታ፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን የአረንጓዴ ልማት ጥሪ በመቀበል የሚጠበቅብንን ኃላፊነት ለመወጣት ተዘጋጅተናል- የምክር ቤት አባላት

አዲስ አበባ ሐምሌ 5/2015(ኢዜአ)፦የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን የአረንጓዴ ልማት ጥሪ በመቀበል የሚጠበቅብንን ኃላፊነት ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

በዓለም ላይ እየበረታና እየተስፋፋ የመጣው የሙቀት መጠን መጨመር የሰው ልጆችን ጨምሮ በምድር ላይ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ እየጎዳ የቀውስ ምክንያትም ሆኖ ቀጥሏል።

የዓለምን የተፈጥሮ ዑደት በማዛባት ምድር በውስብስብ ችግሮች እንድትፈተን ዋነኛ ምክንያት እየሆነ የመጣውም የአየር ንብረት ለውጥ መሆኑን በርካታ የዘርፉ ተመራማሪዎች ያስረዳሉ።

ለሰው ልጆች የጤና መቃወስና ለተለያዩ ሕመሞች መዳረግ፤ የድርቅ መፈራረቅና የጎርፍ አደጋ እንዲሁም የግብርና ምርት ለመቀነሱ የአየር ንብረት ለውጥ አንደኛው ምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል።

በተለይም በማደግ ላይ ያሉ አገሮች የችግሮቹ ገፈት ቀማሽ በመሆን የጉዳታቸው መጠን ከዓመት ዓመት እየበረታ ይገኛል።

በመሆኑም ይህንን ዓለም አቀፍ ችግር በመከላከልና በመቋቋም ረገድ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት መርሃ- ግብር ነድፋ ተግባራዊ እንቀስቃሴዎችን ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። 

በዚህም ባለፉት አራት ዓመታትም ከ25 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል በሁለተኛው ምዕራፍም የተሻሉ ውጤቶችን ለማስመዝገብ አገር አቀፍ ንቅናቄ ጀምራለች።

ሁለተኛውን ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም በአፋር ክልል በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል።

በክረምቱ ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ 500 ሚሊየን ችግኞችን በአንድ ጀንበር ለመትከል ዕቅድ የተያዘ ሲሆን፤  ለዚህም 361 ሺህ 415 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቷል።

ለዚሁ አገራዊ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ተሳትፎና ዝግጅት በማስመልከት ኢዜአ ከጥቂት የምክር ቤቱ አባላት ጋር ቆይታ አድርጓል።

ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ ከማል ሃሺ መሀሙድ፤ የአረንጓዴ አሻራ ልማት የሁላችንም የመኖርና የመልማት ዋስትና በመሆኑ በክረምቱ የልማት ሥራችን ዋነኛ አጀንዳ ነው ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የልማት ጥሪ አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት በወከልንባቸው አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ለዕቅዱ ስኬት ሚናችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ አረጋግጠዋል።

ሌላኛው የምክር ቤት አባል አቶ አሽኔ ኦስቲን፤ ለተጀመረው የለውጥ ጉዞ እንዲሁም በየዘርፉ ያሉ እድገቶችን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ፋይዳው ከፍ ያለ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የምግብ ዋስትና መሠረትና የአካባቢ መራቆትን የማልማት ዕቅድ በመሆኑ ዜጎችን ሁሉ የሚመለከት የጋራ ዕቅድ መሆኑንም የምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2050 በዓለም ላይ ከ216 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በችግሩ ሳቢያ ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ የዓለም ባንክ ትንበያ ያመለክታል።

 

   

 

 

 

 

 

  

 

 

 

    

 

 

 

  

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም