ኢትዮጵያ እና ጆርዳን ለስራ የሚሰማሩ ኢትዮጵያውያንን መብት ማስጠበቅ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ ሐምሌ 5/2015(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ጆርዳን ለስራ የሚሰማሩ ኢትዮጵያውያንን መብት ማስጠበቅ የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል።

ከዮርዳኖስ መንግስት ጋር በዮርዳኖስ ለስራ የሚሰማሩ ኢትዮጵያውያንን መብትና ጥቅም የሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ ምክክር መደረጉን የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ ገልጸዋል።

33 ሺህ ኢትዮጵያውያን በሚገኙባት ዮርዳኖስ የዓለም አቀፉን የስራ ድርጅት የሰራተኛና አሰሪ ግንኙነት መስፈርቶች ጨምሮ የደመወዝ ጭማሪ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ የስራ ከባቢ፣ ሕክምና እና ኢንሹራንስን በሚመለከት መወያየታቸውን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የስራ ሰዓትና እረፍትን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ የሁለቱ አገራት ተደራዳሪ ባለሙያዎች ያቀረቡት ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ላይ ከዮርዳኖስ የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ሰራተኛ ጉዳይ ሚኒስትር ዮሴፍ ሻማሊ ጋር ሰፊ ምክክር አድርገን ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።

ስምምነቱ ቀደም ሲል ይላኩ የነበሩት የቤት ውስጥ አገልግሎት ላይ የሚሰማሩ ዜጎች ጨምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰለጠነ እና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል መላክን ለማካተት ያስችላል ነው ያሉት ሚኒስትሯ።

ስምምነቱ ከዚህ ቀደም በጆርዳን የሚገኙ ስራ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያንን እንደሚያካትትና በየዓመቱ የደመወዝ ጭማሪ ማድረግንም ከግዴታ ያስገባ መሆኑን ገልጸዋል።

ስምምነቱ በየጊዜው የሚከሰቱ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት በሁለቱ አገራት መካከል በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ተመስርቶ ክትትል እንደሚደረግበት እና እንደሚታደስ ጠቁመዋል።

ስምምነቱ ከስራ ስምሪት ግንኙነት ባሻገር ኢትዮጵያ ከጆርዳን መንግስትና ሕዝብ ጋር ያላትን የቆየ በእህትማማችነት ላይ የተመሰረተ የዲፕሎማሲ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እና ትብብር የሚያጠናክር መሆኑንም ሚኒስትሯ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም