በምዕራብ ሀረርጌ ዞን በአንድ ጀምበር 55 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሀረርጌ ዞን በአንድ ጀምበር 55 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተጠናቋል
ጭሮ ሐምሌ 5/2015(ኢዜአ)፦ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን በአንድ ጀምበር 55 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መጠናቀቁን የዞኑ ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
ሀምሌ 10/2015 ለሚካሄደው በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ሀገራዊ ንቅናቄ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን 55 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል አስፈላጊው ዝግጅቶች መደረጋቸውን የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ አልዪ ዳዲ ገልፀዋል፡፡
በበጋው ወቅት በህዝብ ተሳትፎ በምእራብ ሀረርጌ ዞን ከፍተኛ ተራራማ አካባቢዎች ላይ የተገነባውን የተፋሰስ ልማት እርከኖች በችግኝ በማልበስ የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል፡፡
ምክትል ኃላፊው አክለውም የችግኝ ተከላው ለዞኑ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥና አየር ንብረት ተስማሚ የሆኑ የተለያዩ ችግኞችን በመትከል የድርቅ ተጋላጭ ወረዳዎችን ችግር ለመቀነስ ከፍተኛ አበርክቶ አንዳለውም ጠቁመዋል፡፡
አረንጓዴ አሻራ በህዝብ ንቅናቄ በየአመቱ መተግበር ከጀመረ ወዲህ እንደ ቡርቃ ዲንቱ፣ ሀዊጉ ዲናና ጉምቢ ቦርደዴ ወረዳዎች ዝናብ ማግኘት መጀመራቸውንና የተገኘው ለውጥ ድርቅን በማስቀረት የግብርና ምርት መጠን መጨመር እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን አክዋል፡፡
ከሚተከሉት የችግኝ አይነቶች መካከል ከደን ተክሎች ባሻገር አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ቡና ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በእለቱም ከዞኑ 15 ወረዳዎችና 5 ከተማ አስተዳደሮች ከ2 ሚሊዮን በላይ ህብረተሰብ የንቅናቄው ተሳታፊ እንደሚሆን አቶ አልዪ ዳዲ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
በ5 መቶ ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ጀምበር የመትከል ተሳትፎ ላይ ከሚሳተፉ ተቋማት መካከል የጭሮ ከተማ መንገድና ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሀመድ ኡመር ችግኝ በመትከል የተስተካከለ የአካባቢ አየር ለመተንፈስ ደከመን አንልም ብለዋል፡፡
እንደሀገር በሚካሄደው የችግን ተከላ ንቅናቄ ሁሉም ዜጋ መሳተፉ የሚፈለገውን ለውጥ በቅርብ እንሚመጣ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመው ተራራማውን የሀረርጌ ምድር አረንጓዴ የማልበስ ርብርቡን እያፋጠኑት መሆኑን ተናግረዋል፡፡