በአዲስ አበባ ከተማ የ109 የአሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የስራ ፈቃድ ተሰረዘ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ከተማ የ109 የአሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የስራ ፈቃድ ተሰረዘ
አዲስ አበባ ሐምሌ 5/2015(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ የ109 የአሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የስራ ፈቃድ መሰረዙን የአዲስ አበባ የስራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
እርምጃ የተሰወደባቸው ኤጀንሲዎች በሀገር ውስጥ ሰራተኞችን በማገናኘት ላይ የሚሰሩ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡
የቢሮው የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ፍስሀ ጥበቡ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ከኤጀንሲዎች የስራ ስምሪት ጋር በተያያዘ ከህብረተሰቡ ቅሬታ ሲቀርብ መቆየቱን ተናግረዋል።
ቢሮው ቅሬታውን መሰረት በማድረግ ሰፊ የክትትል ስራ ማከናወኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ህጋዊ አሰራር ሂደቶችን በመጣስ ሲሰሩ የነበሩ 109 የአሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የስራ ፈቃድ እንዲሰረዝ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
እርምጃ የተወሰደባቸው ኤጀንሲዎች የአሰሪና ሰራተኛ ቅጥር በሚመለከት የተቀመጠውን መስፈርት ሳያሟሉ አገልግሎት ሲሰጡ የተገኙ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
የመንግስትም ሆነ የግል ቀጣሪ ተቋማት ሰራተኞችን ከኤጀንሲዎች በሚቀጥሩበት ወቅት አስፈላጊውን ማጣራት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።