ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞን ለማፋጠን የታችኛውን መዋቅር የአሰራር ሂደት የመደገፍ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል -ከፍተኛ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞን ለማፋጠን የታችኛውን መዋቅር የአሰራር ሂደት የመደገፍ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል -ከፍተኛ አመራሮች
ሚዛን አማን ሐምሌ 5/ 2015 (ኢዜአ)፡- ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞን ለማፋጠን የታችኛውን መዋቅር የአሰራር ሂደት የመከታተልና የመደገፍ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች አስታወቁ።
አመራሮቹ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ የልማት እንቅስቃሴን ተመልክተዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሐመድ በወቅቱ እንዳመለከቱት፤የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ አመራሮች በየአካባቢው እየተሰሩ ያሉ ተግባራትን ለመደገፍ ተሰማርተዋል።
ይህም የታችኛውን መዋቅር የአሰራር ሂደት እየተከተሉ ማበረታታትና ክፍተቶች ካሉ ከሕግና ፖሊሲ አንጻር ታይተው እንዲስተካከሉ ለመደገፍ መሆኑን አስረድተዋል።
በተለይ በየአካባቢው እየተተገበሩ ያሉ አርአያነት ያላቸው ሥራዎችን ከምልከታ በኋላ ወደ ሌሎች ስፍራዎች ለማስፋፋት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ዶክተር አህመዲን፤ በሸካና ቤንች ሸኮ ዞኖች እስካሁን በሀገራዊ ንቅናቄ መሠረት በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት እና በሥራ ዕድል ፈጠራ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ተመልክተናል ብለዋል ።
የሥራ ባህል እንዲቀየርና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲስፋፋ ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ መንግሥት ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች እንዲተገበሩ ክትትል እንደሚያደርጉ አመላክተዋል።
የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ አመራር ክትትልና ድጋፍ ቀጣይነት እንደሚኖረው የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በዚህ ተግባር የኢትዮጵያ ዕድገት ተፋጥኖ ብልጽግና እንደሚረጋገጥ ተናግረዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሰግድ ጌታቸው በበኩላቸው፤ የሥራ ድጋፍ ስምሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ የተናገሩትን ታች ወርዶ የመከታተል ቃል የሚያጸና ነው ብለዋል።
የብልጽግናን ግብ ሊያረጋግጡ የሚችሉ አበረታች እንቅስቃሴዎች አሉ፤ መልካም ጅምሮችን ማስፋፋትና ከፍ ማድረግ ላይ አተኩረን የእገዛ ሥራ እንደ መንግሥት እንሰራለን ነው ያሉት።
በተለይ በቴፒና በሚዛን አማን ከተሞች በኢንተርፕራይዝ ሥራ ዘርፍ የግብዓት፣ የማምረቻና መሸጫ ቦታ ማመቻቸት ከተቻለ፡ ኤክስፖርት እስከ ማድረግ አቅም ያላቸው በእንጨት ሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ማኅበራትን እንደጎበኙ ተናግረዋል።
በዚህም አካባቢው ያለውን ምቹ የተፈጥሮ ሀብት ወደ ኢኮኖሚ በመቀየር በሀገር አቀፍ ደረጃ ትልቅ ለውጥ ማስመዝገብ እንዲችሉ ለተደራጁ ማኅበራት ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።
የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሚዛን አማን ከተማ የልማት ሥራዎችን የጎበኙ ሲሆን፤ በምልከታቸው ውስጥ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች የሚፈቱበትን አቅጣጫ መጨረሻ ላይ በጋራ እንደሚያስቀምጡ ተመላክቷል።