የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላው ስኬታማ እንዲሆን ሁላችንም በትብብር እንሰራለን- ዶክተር ጌታቸው መለሰ - ኢዜአ አማርኛ
የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላው ስኬታማ እንዲሆን ሁላችንም በትብብር እንሰራለን- ዶክተር ጌታቸው መለሰ
ደሴ ሐምሌ 4/2015 (ኢዜአ) የአንድ ጀምበር አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ስኬታማ እንዲሆን ሁላችንም በትብበር እንሰራለን ሲሉ የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ጌታቸው መለሰ አስታወቁ።
የፌዴራል መንግስት የከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ ለክረምት ተከላ የተዘጋጀን ችግኝና ሌሎች የልማት ስራዎችን ተመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ኮምሽነር ዶክተር ጌታቸው መለሰ በወቅቱ እንዳሉት በደቡብ ወሎ ዞንና አካባቢው የልማት ስራዎችን በመመልከት መልካሙን ለማስቀጠል፣ ክፍተቶችን ደግሞ በጋራ ለመሙላት ታስቦ እየተሰራ ነው።
በተለይ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት፣ ችግኝ ተከላና ሌሎች የልማት ሥራዎች ያሉበትን ሁኔታና ቅደመ ዝግጅት ለመመልከት ወደ ዞኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በሰጡት መመሪያ መሰረት ለክረምት ስራዎች ውጤታማነት ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን የአመራሩና የህብረተሰቡ የልማት ተነሳሽነት የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ሐምሌ 10 በአንድ ጀምበር የሚተከለው 500 ሚሊዮን ችግኝ በስኬት እንዲጠናቀቅ በተደራጀ መንገድ ሁሉም የድርሻቸውን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል።

''በደቡብ ወሎ ዞንም በአንድ ጀምበር 48 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ለተያዘው እቅድ ስኬታማነት የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር ተባብረን እንሰራለን" ሲሉ ዶክተር ጌታቸው አስታውቀዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አህመድ ጋሎ በበኩላቸው እንዳሉት በዞኑ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር 273 ሚሊዮን ችግኝ በ43 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ይተከላል።
ከሚተከለው መካከል 48 ሚሊዮን ችግኝ ሐምሌ 10 በአንድ ጀምበር በ4 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለመትከል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በተከላው ከ970 ሺህ በላይ የሰው ሃይል ለማሳተፍ ከወዲሁ ተዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
ለውጤታማነቱ የፌዴራል ከፍተኛ የስራ ሀላዎች በዞኑ መገኘት አስተዋጾ እንዳለው ጠቁመው "ተጋግዘንና ተደጋግፈን እናሳካዋለን" ብለዋል።
'ከፍተኛ 'የስራ ሀላፊዎቹ የወረዳውን የልማት ስራ በማገዝ ለውጤታማነታችን ጉልህ ያበርክታሉ'' ያሉት ደግሞ የቃሉ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙህዲን አህመድ ናቸው።
"ከስራ ሀላፊዎቹ ትምህርት በመውሰድ፣ አስተያየት በመቀበልና በመተጋገዝ ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት በቁርጠኝነት እንሰራለን "ብለዋል።
''በወረዳው በአንድ ጀምበር ለምንተክለው 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ችግኝ ያደረግነውን ቅደመ ዝግጅትም ተመልከተው ጉድለቶቻችን አሳይተውናል፤ እናስተካክላለንም'' ሲሉም አክለዋል።
'ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ወደ ወረዳችንን መምጣታቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩን የፓርላማ ንግግር በተግባር ከማሳየቱ ባለፈ ለልማት ስራዎች እንድንነሳሳ አድርጎናል'' ያሉት ደግሞ በቃሉ ወረዳ የ030 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ፋጡማ ሰይድ ናቸው።
በክረምት በጎ ፍቃድ የአካባቢው ትምርት ቤት ማስፋፊያ ብሎክ ግንባታ በመጀመሩ መደሰታቸውን ጠቁመው፤ በአንድ ጀምበር የሚተከለው ችግኝ በስኬት እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።
በመስክ ምልከታው የቆላ ፍራፍሬ ልማት፣ ችግኝ ጣቢያና ሌሎችም የልማት ስራዎች ተጎብኝተዋል።