ቀጥታ፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበ ቡና ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን በላይ ዶላር ገቢ ተገኝቷል - የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን

አዲስ አበባ ሐምሌ 4/2015 (ኢዜአ) በተጠናቀቀው 2015 በጀት ዓመት ከ240 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን በላይ የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ።

ባለሥልጣኑ በበጀት ዓመቱ የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ጥራትን ለማስጠበቅ፣ ግብይትን ለማዘመን፣  ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥና እና የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለመጨመር የተከናወኑ ስራዎችን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር፤ በበጀት ዓመቱ 240 ሺህ 369 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን በላይ ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።

ገቢው በዕቅድ ዘመኑ ለማግኘት ከታቀደው 1 ነጥብ 8 ቢሊየን በላይ ዶላር ያነሰ መሆኑን ተናግረዋል።

ሳዑዲ-አረቢያ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ፣ ኮሪያ፣ ቤልጂዬም፣ ጃፖን፣ ዩናይትድ ዓረብ ኢምሬትስ፣ ቻይና፣ ጣሊያን እና ሱዳን 80 ከመቶ በላይ የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻ አገራት መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ለገቢው መቀነስ በዓለም የቡና ገበያ መቀዛቀዝና የቡና ዋጋ ቅናሽ ማሳየትን እንደ ምክንያት ያነሱት አቶ ሻፊ፤ የኢትዮጵያን ቡና ተፈላጊነት ማስቀጠል መቻሉን አብራርተዋል።

የቡና ገበያ ስትራቴጂ በመንደፍ፣ ነባር ገበያዎችን ከማስቀጠል ባለፈ አዳዲስ ገበያዎችን በማፈላለግ በአሜሪካና ዱባይን ጨምሮ በተለያዩ የንግድና ኤግዚቢሽኖች መሳተፍ እንደተቻለም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ቡና የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማሳደግም ያለ አግባብ ተጠቃሚ ደላሎችን ማስወጣት ያስቻለ የቀጥታ ንግድ ግንኙነት ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉ ገቢን ለማሻሻል እገዛ ማድረጉን  ገልጸዋል።

አምራችን ላኪንና አቅራቢን በቀጥታ የሚያገናኝ ስርዓት በመፈጠሩም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማሳደግ መቻሉን ነው ያነሱት።

የቡና ንግድ አገልግሎትን ለማሳለጥ ከተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ተገልጋዮች በቴክኖሎጂ የታገዘና ባሉበት ቦታ አገልግሎት የሚያገኙበት ስርዓት ተዘርግቷል ብለዋል።

ህገወጥ የቡና ንግድ ላይ በተወሰደው እርምጃም ከክልል የቁጥጥር ግብረ ኃይልና ባለድርሻ አላት ጋር በመቀናጀት የግብይት ጊዜ ያለፈበትና በኬላ ቁጥጥር የተያዘን ቡና ገቢ ማድረግ እንደተቻለም ገልጸዋል።

በቡና ንግድ ላይ በተደረገ የቁጥጥር ስራና ከቅጣት የተገኘ ከ192 ሚሊየን በላይ ብር ለመንግስት ገቢ መደረጉን አብራርተዋል።

ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎትና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ባደረጉት ትብብር በቡና ኮንትሮባንድ የተሳተፉ 11 የኬላ ተቆጣጣሪዎች  በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በሕግ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በ2014 በጀት ዓመት 302 ሺህ ቶን ቡና ወደ ተለያዩ ሀገራት በመላክ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷን የባለስልጣኑ መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም