ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ባለድርሻ አካላት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ ቀረበ

አሶሳ ሐምሌ  4 /2015(ኢዜአ)   በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የትምህርት ቤቶች ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ባለድርሻ አካላት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ጥሪ አቀረበ፡፡

የቢሮው ሃላፊ አቶ ቢኒያም መንገሻ  ሐምሌ 8 ቀን 2015 ዓ.ም “ትምህርት ለትውልድ” በሚል ቃል የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት መሻሻያ ንቅናቄ አስመልክቶ ዛሬ በአሶሳ ከተማ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸው እንዳመለከቱት፤ በክልሉ ባለፉት ዓመታት ትምህርት ቤቶችን ለማስፋፋት በተደረገ ጥረት 601 አንደኛ እና 92 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡

ከአጠቃላይ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁት ግን 4 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ሐምሌ 8 ቀን  2015 ዓ.ም  የሚካሄደው  ንቅናቄ  የትምህርት ቤቶቹን ደረጃ እና ጥራት ለማሻሻል ያለመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አያይዘውም በክልሉ ባለፉት ዓመታት በነበረው ችግር ጉዳት ከደረሰባቸው 287 ትምህርት ቤቶች መካከል 107ቱ ጥገና ተደርጎላቸው መልሰው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አመልክተዋል፡፡

ተጠግነው ለአገልግሎት ከበቁት መካከል 33ቱ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተከናወኑ መሆናቸውን አመልክተው፤ በጠቅላላው ለጥገናው 37 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በ2016 የትምህርት ዘመን ትምህርት ቤቶችን ሙሉ በሙሉ ጠግኖ ስራ ከማስጀመር ባሻገር የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል በተለያዩ ችግሮች ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑትን ከ50 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ መታቀዱን ሃላፊው አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ የተማሩ ምሁራን፣ ባለሃብቶች፣ ህብረተሰቡ እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በንቅናቄው ላይ በመሳተፍ ለትምህርት ቤቶች መሻሻል እና ጥራት መጠበቅ ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ አቶ ቢኒያም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም