ቀጥታ፡

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማሳለጥ እየተሰራ ነው - የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ትሬድ ግሩፕ

አዲስ አበባ ሐምሌ 4/2015(ኢዜአ)፦የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ትሬድ ግሩፕ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማሳለጥ እየሰራ መሆኑን የተቋሙ ሊቀ-መንበር የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለፁ።

“አፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ትሬድ ግሩፕ” (ኢ - ትሬድ ግሩፕ) የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራትን ፍላጎት መሠረት በማድረግ የንግድ ልውውጥን ለማሳለጥ የተቋቋመ ተቋም ነው።

ተቋሙ በተለይም በአፍሪካ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማዕቀፍ የንግድ እሴት ሰንሰለት በማጠናከር የአህጉሪቱን ምጣኔ ኃብታዊ እድገት ለማፋጠን ትኩረት አድርጓል።     

ተቋሙን በሊቀ-መንበርነት በመምራት ላይ የሚገኙት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በአፍሪካ የዲጂታል የንግድ ሥርዓትን ለማሳለጥ እየተሰራ መሆኑን ለኢዜአ ገልፀዋል። 

በዚህም በተለይም በጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ የንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታዎች ለማመቻቸት እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በአፍሪካ የሚመረቱ ምርቶች በአህጉሪቱ ሰፊ የገበያ ዕድል እንዲያገኙና በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ ጉልህ አስተዋጽዖ እንዲኖራቸው ለማድረግ ተቋሙ ትኩረት ማድረጉንም ጠቁመዋል። 

ይህንንም እውን ለማድረግና በአፍሪካ የተሰሩ ምርቶችን የሚገበያዩበት ዕድል ለመፍጠር "ሶኩኩ-አፍሪካ" የተሰኘ አህጉራዊ የኤሌክትሮኒክ መገበያያ ሥርዓት መዘጋጀቱን ገልፀዋል። 

በዚህ የኤሌክትሮኒክ መገበያያ ሥርዓት ለመጠቀም በአፍሪካ እስካሁን 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ በማምረትና በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ተቋማት መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

ተቋሙ የኤሌክትሮኒክ መገበያያ ሥርዓቱን ወደ ሥራ ለማስገባት በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል። 

ተቋሙ አፍሪካ ውስጥ ያለውን የገበያ ችግር ለመፍታት በመሠረተ-ልማት፣ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ እንዲሁም በጥናትና ምርምር ላይም ትኩረት ማድረጉን አስረድተዋል።  

በተለይም የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማሳለጥ ከአፍሪካ ሕብረት ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል። 

ተቋሙ በቀጣይ 15 ዓመታት ከ75 እስከ 80 ሚሊዮን የሚደርሱ የአነስተኛና መካከለኛ ተቋማት በዚህ ንግድ ሥርዓት ውስጥ ለማካተት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም