ከመንገድ ፕሮጀክቶች ጎን ለጎን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ተጠናክሮ ይቀጥላል - የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
ከመንገድ ፕሮጀክቶች ጎን ለጎን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ተጠናክሮ ይቀጥላል - የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር
አዲስ አበባ ሐምሌ 4/2015(ኢዜአ):- በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚካሄዱት የመንገድ ፕሮጀክቶች ጎን ለጎን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ገለጸ።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አመራርና ሠራተኞች በሸገር ከተማ አስተዳደር በመና አብቹ ክፍለ ከተማ የችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር አካሂደዋል።
የአስተዳደሩ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ደጀኔ ፍቃዱ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ በ2015 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር እስከ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል አቅዷል።
መርሃ-ግብሩ በአገሪቱ በሚገኙ የተቋሙ አሥር ዲስትሪክቶች፣ 25 የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቶችና 200 በሚጠጉ ፕሮጀክቶች ይካሄዳል ብለዋል።
ይህንንም ተከትሎ በዛሬው ዕለት ከ2 ሺህ በላይ ችግኞች መተከላቸውን ጠቁመዋል።
በአስተዳደሩ የኢንቫይሮመንት ማኔጅመንት ቡድን መሪ ከፍአርጋቸው ካሣሁን በበኩላቸው፤ ባለፉት አራት ዓመታት በየዓመቱ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በተለያዩ ቦታዎች መተከሉን ገልጸዋል።
የተተከሉት ችግኞች በተቋራጭና የመሥሪያ ቤቱ ተቋማት የተለያዩ ሥፍራዎች እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከተተከሉት ችግኞች 75 ከመቶ መፅደቃቸውን ጠቁመዋል።
የችግኞቹ መተከል በመንገዶች ላይ የሚደርሰውን ተፈጥሮአዊ አደጋ በመቀነስ ረገድ አስተዋጽዖ የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የመና አብቹ ክፍለ ከተማ ምክትል አስተዳዳሪ ተሾመ ሆርዶፋ እንደገለጹት፤ የተለያዩ ተቋማት የ2015 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ አሻራቸውን እያኖሩ ነው።
የአካባቢው ማህበረሰብም የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ልምድ ያላቸው በመሆኑ ይህንን ተግባራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።