የመከላከያ ሰራዊታችን የሚሰጠውን ግዳጅ ለመፈጸም ከምንግዜውም በላይ በተሻለ ዝግጁነትና ቁመና ላይ ይገኛል- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሰራዊታችን የሚሰጠውን ግዳጅ ለመፈጸም ከምንግዜውም በላይ በተሻለ ዝግጁነትና ቁመና ላይ ይገኛል- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ ሐምሌ 4/2015 (ኢዜአ)፦ "የመከላከያ ሰራዊታችን የሚሰጠውን ግዳጅ ለመፈጸም ከምንግዜውም በላይ በተሻለ ዝግጁነትና ቁመና ላይ ይገኛል" ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ይህን ያሉት “ምንጊዜም ለመዘመንና ለድል አድራጊነት እንዘጋጅ” በሚል መሪ ሃሳብ የዳሎል ማዕከላዊ እዝ ዓመታዊ ክብረ በዓል በጅማ ከተማ በተከበረበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ነው።
በመልዕክታቸውም የዳሎል ማዕከላዊ እዝ በእሳት የተፈተነና ለአገር ሉዓላዊነት አኩሪ ጀግንነት የከፈለ እዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የእዙ አባላትም በቀጣይም በላቀ የግዳጅ አፈጻጸም ግዳጃቸውን ለመፈጸም ዝግጁነታቸውን ይበልጥ ሊያጠናክሩ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡
በአሁኑ ወቅት የመከላከያ ሰራዊቱ በዘመናዊ ትጥቅ በመደራጀት የሚሰጠውን ግዳጅ ለመፈጸም ከምንግዜውም በላይ በተሻለ ዝግጁነትና ቁመና ላይ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡
የሰራዊቱ ዋነኛ ዓላማ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት መጠበቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ተልዕኮውንም በብቃት ይወጣል ብለዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊቱ የጀግንነት ማዕከል የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ የመከላከያ ሰራዊቱን ስም በሀሰት በማጠልሸት የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማስፈጸም የሚሰሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ብለዋል፡፡
የእነዚህ አካላት ዋነሻ ዓላማም ከባዕዳን ተልዕኮ በመቀበል ኢትዮጵያን ማፍረስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መከላከያ ሰራዊቱ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ ባከናወናቸው ተግባራት በተለያዩ ክልሎች በሀሰተኛ መረጃዎች ተደናግረው በህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ተሰማርተው የነበሩ በርካታ አካላትን ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም የመከላከያ ሰራዊቱ የኢትዮጵያ ህልውና እና ሉዓላዊነት በማስከበር ረገድ የትኛውንም ግዳጅ በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡