በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል 361 ሺህ 415 ሄክታር መሬት ዝግጁ ሆኗል-የግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል 361 ሺህ 415 ሄክታር መሬት ዝግጁ ሆኗል-የግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ሀምሌ 4/2015(ኢዜአ)፡- ሐምሌ 10 ቀን 2015 በኢትዮጵያ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ለተያዘው እቅድ 361 ሺህ 415 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ፤ አጠቃላይ ዝግጅቱን በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም በአንድ ጀንበር ለሚካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 9 ሺህ 500 የመትከያ አካባቢዎች መለየታቸውን ገልጸዋል።
ለ500 ሚሊዮን ችግኞች መትከያ 361 ሺህ 415 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱንም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
በዕለቱ በየአካባቢው የሚደረጉ የችግኝ ተከላዎችን ከስፍራው በቀጥታ ለዓለም ህዝብ ተደራሽ ለማድረግ የካርታና GREENLEGACY.ET የዌብ ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል።
ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ከስፔስ ሳይንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር 9 ሺህ 500 ቦታዎችን በካርታ የማካተትና ድረገፅ በማበልፀግ ወደ ስራ መገባቱን ፕሮፌሰር እያሱ ተናግረዋል።
በእለቱ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በሁሉም ቦታዎች በተመደቡ ባለሙያዎች ወደ ማዕከል ሁነቱ የሚደርስ መሆኑንም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ለተያዘው እቅድ ዜጎች ሁሉ በነቂስ ወጥተው አሻራቸውን እንዲያኖሩ ሚኒስትር ዴኤታው ጥሪ አቅርበዋል።
በእለቱ ከ25 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በችግኝ ተከላው እንደሚሳተፍ ጠቅሰው እቅዱ የሚሳካ መሆኑንም የጸና እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ከሚተከሉ ችግኞች መካከል 60 በመቶው ለጥምር ደን ግብርና፣ 35 በመቶው ለተፋሰስ ልማትና ለደንሽፋን እንዲሁም አምስት በመቶው ለከተማ ውበት የሚያገለግሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያውያን ችግኞችን ወደ መትከያ ቦታ በጥንቃቄ በማድረስ፣ ማስቀመጫ ፕላስቲኮችን በጥንቃቄ በማስወገድ ኢንዲተክሉና ለተያዘው ግብ እርብርብ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
በጥንቃቄና በሙያዊ መንገድ ችግኞች እንዲተከሉ የሚያግዙ ባለሙያዎችም በሁሉም አካባቢዎች የሚሰማሩ መሆኑም ተጠቅሷል።
ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተደረገው ጥሪ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ትግበራ በተግባር የሚታይበት ይሆናል።