በቡና ልማት ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ለማድረግ የተሰራው ሥራ አመርቂ ውጤት አስገኝቷል - የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን - ኢዜአ አማርኛ
በቡና ልማት ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ለማድረግ የተሰራው ሥራ አመርቂ ውጤት አስገኝቷል - የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን
አዲስ አበባ ሀምሌ 4/2023(ና)፡- በ2015 በጀት ዓመት በቡና ልማት ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ለማድረግ የተሰራው ሥራ አመርቂ ውጤት ማስገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት የሥራ አፈፃጸም አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር በሰጡት መግለጫ በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ከ240 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለውጭ ገበያ ቀርቧል ብለዋል።
ሳዑዲ-አረቢያ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ፣ ኮሪያ፣ ቤልጄየም፣ ጃፓንና ዩናይትድ ዓረብ ኢምሬትስ የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻ አገራት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ ለውጭ ገበያ ከቀረበው የቡና ምርት ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ መገኘቱንም ነው የገለጹት።
ወደ ውጭ ከተላከው የቡና ምርት የተገኘው ገቢም ከዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ መቀዛቀዝና ሌሎች ተፅዕኖዎች አኳያ የሚበረታታ ውጤት ነው ብለዋል።
አያይዘውም በ2015 በጀት ዓመት በቡና ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ለማድረግ የተሰሩት ሥራዎች አመርቂ ውጤት ማስገኘቱንም ጠቁመዋል።
በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበው የቡና ምርት 1 ነጥብ 24 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የባለሥልጣኑ መረጃ ያሳያል።