ከተሞችን ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል--አቶ አህመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
ከተሞችን ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል--አቶ አህመድ ሽዴ
ባህር ዳር ሐምሌ 3/2015(ኢዜአ) የከተሞችን ፈጣን እድገት በማስቀጠል ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ የፌደራል መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ።
የፌደራልና የባህር ዳር ከተማ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮቹ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የመሰረተ ልማትና የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሥራዎችን በመጎብኘት ችግኝ ተከላ አከናውነዋል።
የፌደራል የክረምት የልማት ሥራዎች ድጋፍና ክትትል ቡድን መሪና የገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እንዳሉት በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገችው ባህር ዳር ከተማ ፈጣን እድገቷ ለሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ምሳሌ የሚሆን ነው።
"በከተማዋ የሚስተዋሉ የኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ የሌማት ቱሩፋትና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ይበልጥ ተመራጭ እንዳደረጓት በጉብኝታችን አረጋግጠናል" ብለዋል።
የፌደራል መንግስትም እንደ ገበታ ለሃገር፣ አንድነት እና ሸገር ፓርኮችን እንዲሁም ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ለከተሞች እድገት አርአያነት ያለው ተግባር እየፈጸመ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይም በዓለም ባንክና በፌደራል መንግስት የገንዘብ ወጪ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችን በስፋት በማከናወን ለከተሞች ብልጽግና የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አረጋግጠዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በበኩላቸው የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለባህር ዳር ከተማ ልዩ የልማት ዓመት ነው ብለዋል።
ለዚህም መስተዳድሩ ለከተማዋ የመሰረተ ልማት ግንባታ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በመበጀት ትላልቅ የመንገድ፣ የአረንጓዴ ልማትና ሌሎች የልማት ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
አያይዘውም የባህር ዳር ከተማን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት በጃፓን መንግስት ከ650 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ በተለምዶ "አባይ ማዶ" የሚባለው አካባቢ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋም በአሁኑ ወቅት መጠናቀቁን ገልፀዋል።
የፌደራልና የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር አመራሮች ከጉብኝታቸው ጎን ለጎን በባህር ዳር ከተማ "ቤዛዊት" በተባለ አካባቢ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።
ከእዚህ ጎን ለጎን በከተማዋ የሚገኙትን የጣና ፎረም ፓርክ፣ የሚሊኒየም ትምህርት ቤትን እና ሌሎች የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።