የትምህርት ሚኒስቴር በሀገሪቱ በትምህርት ዘርፍ የተሻለ እምርታ ለማምጣት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ሚኒስቴር በሀገሪቱ በትምህርት ዘርፍ የተሻለ እምርታ ለማምጣት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቀረበ
ሀዋሳ ሐምሌ 03 ቀን 2015 (ኢዜአ)፡- በሀገሪቱ በትምህርት ዘርፍ የተሻለ እምርታ ለማምጣት በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ የትምህርት ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።
“ትምህርት ለትውልድ" በሚል መሪ ቃል በሲዳማ ክልል የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት ለማሻሻል የተዘጋጀ ክልላዊ ንቅናቄ መድረክ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።
በዚህ ወቅት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ እንዳሉት በትምሀርት ጥራት ላይ ያጋጠመውን ፈተና ለማሻሻልና ወደ ሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ ንቅናቄው እጅግ አስፈላጊ ነው።
ባለፉት ዓመታት ለትምህርት መስፋፋትና ተደራሽነት በየደረጃው በተሰራው ልክ ለትምህርት ጥራት ትኩረት ተሰጥቶ ባለመሰራቱ ችግር ማጋጠሙን ጠቁመዋል።
ለጥራት መጓደል መንስኤ ከሆኑት ብዙ መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ አለመሆንን ጠቅሰዋል።
በዚህ ረገድ በሀገሪቷ ካሉ 50 ሺህ የመጀመሪያ፣ መለስተኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል 86 በመቶ የሚሆኑት ከደረጃ በታች መሆናቸውን አመላክተዋል።
በመሆኑም ሚኒስቴሩ እንደ ሀገር የገጠመውን የትምህርት ስብራት ለመጠገን የተለያዩ ሪፎርሞችን በማዘጋጀት እየሰራ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
በየትምህርት ቤቱ ተምረው በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ አካላት፣ ባለሀብቶችና የየአካባቢው ማህበረሰብ ትምህርት ቤቶች የሚያስፈልጓቸውን የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ መብራት፣ መጸዳጃ ቤቶች፣ ቤተ ሙከራና ቤተ መጸሀፍትና ሌሎች መሰረተ ልማት ለማሟላት ርብርብ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በትምህርት ጥራት ላይ በትኩረት ባለመሰራቱ ችግሮች እያጋጠሙ ነው ብለዋል።
ከዚህ በመማር በተለይ ሀገር በትውልድ ቅብብሎሽ የሚሰራ በመሆኑ በታሪክ ውስጥ የማይረሳ አሻራ ለመጣል ሁሉም የተጣለበትን አደራ እንዲወጣ አስገንዝበዋል።
የሲዳማ ክልል ርእሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው በክልሉ በትምህርት ተሀድሶ መርሐ ግብር ሁሉንም ህብረተሰብ በማሳተፍ ተጨባጭ ውጤት እየተገኘ መምጣቱን ጠቁመዋል።
''ትምህርት ለትውልድ'' ንቅናቄ ይህንን ይበልጥ አጠናክረን ለመቀጠል በር ከፋች በመሆኑ ለተግባራዊነቱ የክልሉ መንግሥት አበክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ብልጽግና የሚረጋገጠው በሰለጠነ የሰው ኃይል እንደመሆኑ መጠን ብቁ ዜጋ ለመፍጠር የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ በክልሉ እውን ለማድረግ ሰፊ ርብርብ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ ባራሶ በክልሉ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለይ በዚህ ዓመት ባለሀብቱን፣ የመንግሥት ሰራተኞችንና በየደረጃው የሚገኘውን የክልሉን ህዝብ በማስተባበር 100 ደረጃቸውን የጠበቁ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ 83ቱን ማሳካት መቻሉን አውስተዋል።
በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ውስጥም በክልሉ ሁሉም የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት በገጠርና በከተማ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ይሰራል ብለዋል።
በመድረኩ ከተሳተፉ ባለሀብቶች መካከል አቶ አሰፋ ዱካሞ በሰጡት አስተያየት የሲዳማ ክልል መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት ባደረገላቸው ጥሪ መሠረት ለትምህርት መስፋፋት ጠንካራ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማውጣት በአምስት ወረዳዎች አምስት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ለክልሉ መንግሥት እያስረከቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ በ2016 በጀት አመት የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት ለማሻሻል የተዘጋጀ የእቅድ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።
በመርሀ ግብር ላይ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንታዬ ከበደ፣ በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት ዘርፍ አመራሮች ተሳትፈዋል።