የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ከቻይና የሕዝብ ደህንነት ምክትል ሚኒስትር ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ከቻይና የሕዝብ ደህንነት ምክትል ሚኒስትር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ሐምሌ 3/2015(ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ፤ የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት የቻይና የሕዝብ ደህንነት ምክትል ሚኒስትር ቼን ሲዩዋን ከተመራ ልዑካን ቡድን ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ውይይት አድርገዋል።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ በቅርቡ ቻይናን በጎበኙበት ወቅት የሁለቱ አገራት የፖሊስ ተቋማት በተለያዩ ዘርፎች ትብብራቸውን ለማጠናከር፣ የሁለትዮሽ የከፍተኛ ኃላፊዎችና የባለሙያ ቡድን የጋራ መድረክ ለመፍጠር፣ ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል፣ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ፣ የኢትዮ-ቻይና የሕግ ማስከበር ትብብር ማዕከልን በኢትዮጵያ ለማቋቋምና የህግ አስከባሪ አካላትን አቅም ለማጠናከር ውይይት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር የቆየ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላት ገልጸው ሁለቱ አገራት በፀጥታ ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከርና ፖሊስ ለፖሊስ ትብብርን ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የቻይና የሕዝብ ደህንነት ምክትል ሚኒስትር ቼን ሲዩዋን በበኩላቸው ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥ ገልጸው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እያስገነባ ያለውን የፎረንሲክ የልህቀት ማዕከል በማቴሪያል፣ በአቅም ግንባታ እና በቴክኖሎጂ ለማገዝ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።
በምክክራቸውም የሁለቱ አገራት የፖሊስ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ባደረጉት የመጀመሪያ ስብሰባ የፖሊስ አመራሮች፣ የኦፊሰሮች፣ የከፍተኛ ባለሙያዎች ልምድ ልውውጥ በማድረግ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
በቀጣይም እ.ኤ.አ በ2025 የሁለቱ አገራት የፖሊስ ተቋማት በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ በቻይና የሁለትዮሽ የጋራ መድረክ ለማካሄድ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል።