በፈረንሳይና ስፔን የሚኖሩ ዳያስፖራዎች የትውልድ አገራቸውን ገጽታ ለማስተዋወቅና ተሳትፏቸውን ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በፈረንሳይና ስፔን የሚኖሩ ዳያስፖራዎች የትውልድ አገራቸውን ገጽታ ለማስተዋወቅና ተሳትፏቸውን ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገለጹ
አዲስ አበባ ሐምሌ 3/2015(ኢዜአ):-በፈረንሳይና ስፔን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የትውልድ አገራቸውን ገጽታ ለማስተዋወቅና ተሳትፏቸውን ለማሳደግ እንደሚሰሩ አስታወቁ።
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የተውጣጣ የልዑካን ቡድን በፈረንሳይና አካባቢው ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አደረጃጀቶች ጋር ውይይት አድርጓል።
በውይይቱ ላይ ከፈረንሳይ እና ስፔን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አመራሮች፣ በሁለቱ አገራት ያሉ የዲፌንድ ኢትዮጵያ አባላት፣ በየአገራቱ ከሚገኙ የተለያዩ የማህበረሰብ አመራሮች፣ምሁራን፣ የንግድ ማህበረሰብ አባላት፣የሃይማኖት መሪዎች እና የወጣት ማህበራት ተገኝተዋል።
የዳያስፖራውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ምክክር መደረጉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታውቋል።
ዳያስፖራው ከአገሩ ጋር ያለውን ትስስር ለማሳደግ የተዘጋጁ ስልቶችና የዳያስፖራ ተሳትፎን ለማበረታታት በመንግስት የተዘረጉ ምቹ ሁኔታዎች ላይ የተዘጋጁ ሰነዶች ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸው ገልጿል።
ተሳታፊዎችም የዳያስፖራ ወረቶችን በመጠቀም በአገራዊ የልማት ጥሪዎች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ እና የትውልድ አገራቸውን ገጽታ ለማስተዋወቅ እንደሚሰሩ ገልጸው፤ “በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ አዎንታዊ ሚናችንን መወጣታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን” ብለዋል።
ተመሳሳይ መድረኮች በቀጣይነት እንዲዘጋጁ ጠይቀዋል።
በፈረንሳይ አስተናጋጅነት የሚካሄደውን እ.አ.አ በ2024 በሚካሄደው 33 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እንደ ትልቅ እድል በመጠቀም የኢትዮጵያ ገጽታ ለማስተዋወቅ የሚያግዙ ስራዎችን እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በውድድሩ ላይ ለሚሳተፉ የኢትዮጵያ አትሌትክስ ቡድን አባላት እና በመላው አውሮፓ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ፓሪስ በመገኘት ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡