የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ "ዲጂታል መታወቂያ ለፋይናንስ ዘርፍ" የተሰኘ ፕሮጀክት ትግበራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ "ዲጂታል መታወቂያ ለፋይናንስ ዘርፍ" የተሰኘ ፕሮጀክት ትግበራ ጀመረ
አዲስ አበባ ሐምሌ 3/2015(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር "ዲጂታል መታወቂያ ለፋይናንስ ዘርፍ" የተሰኘ ፕሮጀክት ትግበራ መጀመሩን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የፋይናንስ ዘርፉን ለማዘመንና አስተማማኝነቱን ለማሳደግ የዲጂታል መታወቂያ ትግበራ ዙሪያ ያተኮሩ ሁለት ፕሮግራሞችን ነው ወደ ስራ ያስገባው።
በዚህም የመጀመሪያው መርኃ-ግብር ሁሉም የፋይናንስ ተቋማት ደንበኞቻቸውን በ2016 በጀት ዓመት ወደ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት በማስገባት የተሻለ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።
የመረሐ-ግብሩ ዓላማ ለነዋሪዎች የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋፋትና የተመዝጋቢውን ግላዊ መረጃዎች ጥበቃ ቅድሚያ በመስጠት እና የመረጃ ደህንነትን በማረጋገጥ የሚከናወን መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም እስከ አሁን ድረስ የተሰጡትም ሆነ ከዚህ በኋላ በዚህ ስርዓት የሚሰጡት የዲጂታል መታወቂያዎች፣በሀገሪቱ በሚገኙ በየትኛውም የፋይናንስ ተቋማትም ሆነ ዲጂታል ስርዓቶች ተቀባይነት ይኖራቸዋል ተብሏል።
ሁለተኛው መርሐ-ግብር ደግሞ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሳለጥና የፋይናንስ ስርዓት ደህንነትን ለማስጠበቅ በማቀድ በዘርፉ የኤሌክትሮኒክ ደንበኛህን እወቅ ሂደት ውስጥ የዲጂታል መታወቂያ መጠቀም ነው ተብሏል።
ይህ ሂደት የፋይናንስ አገልግሎቶች ተጠቃሚን ትክክለኛ ማንነት በማረጋገጥ የፋይናንስ ግብይቶች ደህንነትን ለመጠበቅ እና ተያያዥ ስጋቶችን ለመቀነስ ከማስቻሉም ባሻገር ተጠቃሚዎች በአካል መምጣት ሳይጠበቅባቸው በዲጂታል አማራጭ ብቻ ደንበኛ ማድረግ እንደሚያስችል ተመላክቷል።
የብሄራዊ መታወቂያ ትግበራ የገንዘብ መጭበርበርን በመቀነስ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትን በመጨመር እና የተሻሻለ የደንበኞች የማንነት ማረጋገጫ ስርዓት በመዘርጋት የተጠናከረ የፋይናንስ ዘርፍ ለመገንባት ያስችላል ተብሏል።
መርሐ-ግብሮቹ የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለማዘመን እንዲሁም የሀገሪቱን የዲጂታል ኢኮኖሚ ለማጎልበት ለሚደረገው ጎዞ በር ከፋች እንደሚሆኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ አመላክቷል።