ቀጥታ፡

ኢጋድ የሱዳን ኃይሎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ጠየቀ


አዲስ አበባ ሐምሌ 3/2015(ኢዜአ):-  የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም በማድረግ ወደ ድርድር እንዲገቡ አሳሰበ።

ለዚህም ባለድርሻ አካላት የጋራ ጠንካራ ጥረትና ግፊት እንዲያደርጉም ጠይቋል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የአራትዮሽ "ኳርቴት" የመሪዎች ስብሰባ በሱዳን ወቅታዊ ግጭትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ዛሬ ተካሂዷል።

በአራትዮሽ ስብሰባው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ እንዲሁም የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሃሙድ አሊ ዩሱፍና የደቡብ ሱዳን ልዩ መልዕክተኛ ቤንጃሚን ቦል ሜል የየሀገራቱን መሪዎች በመወከል ተገኝተዋል።

የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ፣ የአፍሪካ ህብረት የሰላም፣ ፀጥታና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ኮሚሽነር ባንኮሌ አዲኦዬ፣ የተባበሩት መንግስታት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ የአሜሪካ፣ የዩናይትድ ኪንግደም ተወካዮች እንዲሁም ከሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተወካይ ዩሲፍ ኢዛት ተገኝተዋል።

ኢጋድ ባወጣው መግለጫ፤ በአራትዮሽ ውይይቱ የሱዳንን ችግር በኢጋድ ማዕቀፍ ስር በውይይት ለመፍታት ጥረት መጀመሩንና ኢትዮጵያም ውይይቱን በማስተናገዷ አድንቋል።

የሱዳን ጎረቤት ሀገራት በመጪው ሀሙስ በካይሮ ውይይት እንደሚያደርጉ የጠቆመው መግለጫው፤ ውይይቱም ኢጋድ በሱዳን ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር በአራትዮሽ የመሪዎች የጋራ ጥረት የጀመረውን ግብ ለማሳካት ሚና እንደሚኖረው ጠቁሟል።

በሱዳን በቀጠለው ጦርነት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን፣ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ መፈናቀላቸውንና ይህም ተባብሶ መቀጠሉ እንዳሳሰበው ገልጿል።

አገራት በግጭቱ ለተጎዱ ሱዳናውያን አስፈላጊውን ሰብአዊ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርቧል።

ጎረቤት ሀገራት በጦርነቱ ምክንያት የሚፈናቀሉ ሱዳናውያንን ድንባራቸውምን ክፍት አድረገው እየተቀበሉ መሆናቸውን አድንቋል።

የተኩስ አቁም ስምምነቶች እየተጣሱ መሆናቸውና በካርቱም፣ ዳርፉር፣ ኮርዶፋን እና ሌሎች አካባቢዎች ግጭቶች መባባሳቸው እንዳሳሰበው የጠቀሰው ኢጋድ፤ የሃይማኖትና የጎሳ ጎራን በመያዝ አደገኛ ሁኔታ እንዳይፈጠር ስጋቱን ገልጿል።

 

ኢጋድ በአራትዮሽ የመሪዎች ስበሰባው ለሱዳን ግጭት ወታደራዊ መፍትሔ እንደሌለ መግባባት ላይ መደረሱን በማንሳት ባለድርሻ አካላት ሁለቱን ተፋላሚ ኃይላት ፊት ለፊት ለማወያየት ጠንካራ ጥረት እና ግፊት እንዲያደርጉ ውሳኔ አሳልፏል።

የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች በአፋጣኝ ያለምንም ቅደመ ሁኔታ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉና ከግጭት አባባሽ ተግባራት እንዲታቀቡ የሚያስገድድና ክትትል የሚደረግበት ስምምነት እንዲፈራረሙም ጠይቋል።

ኢጋድ ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም በጅቡቲ ባካሄደው 14ኛ የመሪዎች ጉባኤ የሱዳንን ግጭት መፍትሔ ለማምጣት የኢትዮጵያ፣ የኬኒያ፣ የጅቡቲ እና ደቡብ ሱዳን መሪዎችን ያካተተ የአራትዮሽ "ኳርቴት" የተሰኘ ኮሚቴ ማዋቀሩ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም