ቀጥታ፡

ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል-የምጣኔ ሃብት ምሁራን


አዲስ አበባ ሐምሌ 3/2015(ኢዜአ):- ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር መንግስት የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የምጣኔ ሃብት ምሁራን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰሞኑን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ በመጀመሪያው የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ በርካታ ፈተናዎችን በመቋቋም ወጤት መመዝገቡን መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ለአብነትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በስራ እድል ፈጠራ፣ ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል፣ የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብን ከፍ በማድረግ፤ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትና ገቢን በማሻሻል በኩል የተሻለ ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡

የዋጋ ንረቱ አሁንም ፈተና ሆኖ መቀጠሉን ጠቅሰው፤ መንግስት ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል ችግሩን ለመቀነስ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሃብት ምሁራን፤ የዋጋ ግሽበቱ በምክር ቤቱ ላይ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ መነሳቱ ወቅታዊና ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤት ኃላፊና የምጣኔ ሃብት ምሁር ክቡር ገና፤ የዋጋ ግሽበቱ ዓለም አቀፋዊ ገጽታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በተለይ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ የሸቀጦች ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ መጨመሩን ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ በአገር ውስጥ የተፈጠሩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ቀውሶች ከዓለም አቀፍ ተጽእኖ ጋር ተያይዞ የዋጋ ግሽበቱን እንዳባባሰው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ መንግስት ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል ችግሩን ለመቀነስ እያከናወነ ያለውን ትኩረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው የገለጹት፡፡

አላስፈላጊ ወጪን መቀነስ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው ጉዳይ መሆኑን አንስተው፤ በተለይ የቅንጦት እቃዎች ላይ የተጀመረው ቁጥጥር ሊጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ አቶ ክቡር ገና የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋትም ሆነ ልማትን ለማስቀጠል የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ የሚሆኑት ዘላቂ ሰላም ሲረጋገጥ መሆኑን አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ዘላቂ ሰላም ማስጠበቅ ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ሌላኛው የምጣኔ ሃብት ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ በበኩላቸው የዋጋ ግሽበት ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች እንዳሉት ጠቅሰው፤ ለአብነትም የምግብ ፍጆታዎችን ጨምሮ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሸቀጦች ዋጋ መናር አንደኛው ምክንያት መሆኑን አንስተዋል፡፡


 

ኮንትሮባንድና የጥቁር ገበያ መስፋፋትም ለችግሩ መባባስ በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡ 

ከዚህ አኳያ በመንግስት በኩል በፖሊሲ የተደገፉ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በመተግበር ጭምር ችግሩን ለመቀነስ እያከናወነ ያለው ስራ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ችግሩን ለመቀነስ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ሊጎለብት እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡

ለዚህ ደግሞ ለስራ ምቹ የሆነ ሰላምና መረጋጋት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ይህ ለመንግስት ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉንም ኀብረተሰብ  ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ ወጣቶችን በየአካባቢው ካሉ የልማት አቅሞች ጋር በማስተሳሰር ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም