ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የውጭ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የውጭ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታወቀ
ጎንደር፤ ሐምሌ 3/2015(ኢዜአ)፡- ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ የውጭ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታወቀ።
በዩኒቨርሲቲው የሚማሩ የውጭ ሀገራት ተማሪዎች የእርስ በእርስ ግንኙነትና ልምድ ልውውጥ መድረክ አካሂዷል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ካሳሁን ተገኘ እንዳመለከቱት፤ ዩኒቨርሲቲው ከአራት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት 200 ተማሪዎችን ተቀብሎ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ እያስተማረ ይገኛል፡፡
ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መሠረት ያደረገ የትምህርት ሥርዓት በመዘርጋትና የትምህርት መሰረተ ልማት በማሟላት የውጭ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል።
የውጭ ሀገራት ተማሪዎችን የትምህርት ክፍያ ሥርዓት ወጥ በሆነ መንገድ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችለውን ደንብና መመሪያ አዘጋጅቶ በቅርቡ ስራ ላይ ለማዋል ዝግጅቱን አጠናቋል ብለዋል።
ለዚህም ደረጃውን የጠበቀ የቤተ-ሙከራ፣ የቤተ-መጻህፍትና የኮምፒዩተር ማዕከላትን በማደራጀት ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሕክምናና ምህንድስና ዘርፎች የውጭ ተማሪዎችን ተቀብለው እያሰለጠኑ መሆናቸውን ገልጸው፤ በቀጣይ በሌሎች የትምህርት ዘርፎች ትምህርት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል፡፡
ተማሪዎቹ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱም የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን የሀገራቱን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ዶክተር ካሳሁን ተናግረዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የህክምና ትምህርቱን እየተከታታለ የሚገኘው ደቡብ ሱዳናዊው ተማሪ ኢሊጃህ ሪአክ በሰጠው አስተያየት፤ በቆይታው የኢትዮጵያን ባህልና ታሪካዊ እሴቶች ለመገንዘብ መቻሉን ተናግሯል።
ወደ ሀገሩ ሲመለስ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ግንኙነት ለማጠናከር ጥረት እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡
ከሶማሊያ የመጣውና በዩኒቨርሲቲው የሶስተኛ ዓመት የህክምና ተማሪ የሆነው መሐመድ ኢብራሂም በበኩሉ ''ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገርና ታታሪ ህዝቦች ያላት ናት'' ብሏል፡፡
ከደቡብ ሱዳን የመጣችውና በዩኒቨርሲቲው የሶስተኛ ዓመት የፋርማሲ ተማሪ የሆነችው ኒያዊች ቶይ ''የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የትምህርት እድል በመስጠቱ ታላቅ አክብሮት አለኝ'' ስትል ተናግራለች፡፡
ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በታሪክና በባህል የተሳሰረ ረጅም ዘመናት ያስቆጠረ ታሪክ እንዳላቸው ጠቅሳ፤ ትምህርቷን ጨርሳ ወደ ሀገሯ ስትመለስም ዘመን ተሻጋሪው ግንኙነት እንዲጠናከር አበክራ እንደምትሰራ ገልጻለች፡፡
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት በመደበኛ፣ በማታና በክረምት የትምህርት መርሃ ግብሮች ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያስተናገደ መሆኑን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያሳያል።