በሕገ ወጥ መንገድ ከአገር ሊወጣ የነበረ የውጭ አገር ገንዘብ እና አደገኛ እጽ ከድርጊቱ ተጠርጣሪዎች ጋር ተያዘ - ኢዜአ አማርኛ
በሕገ ወጥ መንገድ ከአገር ሊወጣ የነበረ የውጭ አገር ገንዘብ እና አደገኛ እጽ ከድርጊቱ ተጠርጣሪዎች ጋር ተያዘ
አዲስ አበባ ሐምሌ 3/2015(ኢዜአ):- በሕገ ወጥ መንገድ ከአገር ሊወጣ የነበረ የውጭ አገር ገንዘብ እና አደገኛ እፅ ከድርጊቱ ተጠርጣሪዎች ጋር በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ መያዙን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።
መነሻውን አየር ማረፊያውን አድርጎ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ዱባይ ይወጣ የነበረ 44 ሺህ 440 ዩሮ፣ 11ሺህ 850 የአሜሪካን ዶላር፣ 20 ሺህ 480 ፖውንድ፣ 3 ሺህ 700 ድርሃም፣ 300 የስዊዝ ፍራንክ እና 1 ሺህ 700 የሳውዲ ሪያል መያዙን ፌዴራል ፖሊስ ገልጿል።
ገንዘቡ የተያዘው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የጉምሩክ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የደህንነት ሰራተኞች ባደረጉት ጠንካራ ፍተሻ ከውጭ አገር ዜጎች ተጠርጣሪዎች ጋር መያዛቸውን አስታውቋል።
በተመሳሳይ መነሻውን ብራዚል ሳኦፖሎ አድርጎ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በኩል ወደ ሌሎች አገሮች ሊተላለፍ የነበረ በዱቄት መልክ የተዘጋጀ 17 ነጥብ 9 ኪሎ ግራም ኮኬይን አደገኛ እጽ ከሶስት የውጭ አገር ዜጎች ጋር በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝም ፌዴራል ፖሊስ ጠቁሟል።
በመሰል የወንጀል ድርጊቶች ላይ የፀጥታ አካላት እየወሰዱ ያሉትን ሕጋዊ እርምጃ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመልክቷል።