ቀጥታ፡

የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስራ እየተከናወነ ነው -  የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ጠቅላይ መምሪያ 

አዲስ አበባ ሐምሌ 3/2015 (ኢዜአ)፡- የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ጠቅላይ መምሪያ የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት በብቃት መጠበቅ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስራ እያከናወነ መሆኑን ገለጸ፡፡

መምሪያው ከሁሉም አባል ሀገራት ለተውጣጡ ወታደራዊ ባለሙያዎች በሎጂስቲክስ አቅርቦትና ተልዕኮ አፈፃፀም ላይ የሚሰጠውን የአስር ቀን ሥልጠና ዛሬ ጀምሯል፡፡


 

የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ጌታቸው አሊ እንዳሉት፤ መመሪያው አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካውያን የመፍታት እሳቤ አንዱ አካል ነው፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የቀጣናው ሀገራት ከግጭትና መሰል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚደርስባቸውን ችግር በራሳቸው አቅም ለመፍታት የመሰረቱት የሰላም ተቋም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መምሪያ የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት እንዲወጣ የአባል ሀገራቱን የፖሊስ፣ የሲቪልና ወታደራዊ ባለሙያዎች በተለያዩ ዘርፎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ይሰጣል ብለዋል፡፡

በተቀናጀ ዘመቻ የቀጣናውን ሀገራት ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የሎጂስቲክስ ዘርፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ መምሪያው ለውጤታማ የግዳጅ አፈፃፀም የሚያግዙ ስልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

በምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ጠቅላይ መምሪያ የሎጂስቲክስ ኃላፊ ኮሎኔል አህመድ ኢሳ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካም ሆነ በመላ አህጉሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ሚናዋ የላቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮን በድል በመወጣት፣ የላቀ ተሳትፎ በማድረግ ለአፍሪካውያን አርአያ የምትሆን አገር መሆኗን ተናግረዋል፡፡

በመከላከያ ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር የውጭ ሥልጠና ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶክተር መኮንን አበበ፤ የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ጉልህ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል፡፡


 

በመሆኑም መምሪያው በቀጣናው ግጭትን በመከላከል የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ለሚያደረገው ጥረት የኢትዮጵያ መንግስት አድናቆት እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የሥልጠናው አስተባባሪ ኮሎኔል ሳሙኤል ምዳላ አባላቱ በተሰማሩበት ዘመቻ ግዳጃቸውን በብቃት የሚወጡበትን አቅም የሚያዳብር ሥልጠና ነው ብለዋል፡፡


 

የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን፣ እርስ በርስ በመተባበርና በመተጋገዝ፣ ሰብዓዊ ድጋፍ የሥልጠናው ይዘቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም